ቀጥታ፡

የሠራዊቱን ግዳጅ የመፈጸም አቅም በማጎልበት የሀገርን ሰላምና ደህንነት ማሰከበር ሥራው ይጠናከራል- ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ

ጋምቤላ፤ ኅዳር 17/2016(ኢዜአ) ሀገር መከላከያ ሠራዊት ግዳጅ የመፈጸም አቅም በማጎልበት የሕዝብን ሰላምና ደህነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ ገለጹ።

ለዕዙ የአመራር አባላት የተሰጠው ሥልጠና ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።


 

ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ግዳጅ የመፈጸም ብቃቱን ማጎልበት የዘወትር ተግባር ሆኖ ይቀጥላል።

ሠራዊቱ ግዳጅ የመፈጸም አቅሙን በማጎልበት የሕዝቡን ብሎም የሀገርን ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና አዛዡ ገልጸዋል።

ሠራዊቱ በተሰማራባቸው የግዳጅ ቀጣናዎች ሁሉ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃትና በድል አድራጊነት እየተሻገረ የሕዝቡን ሰላም እያረጋገጠ መሆኑን አመልክተዋል።

በቀለም ወለጋ የሸኔ የሽብር ቡድን ሲፈጥር የነበረውን የጸጥታ ችግር ለማስቆም ሠራዊቱ ባካሄደው የሕግ የማስከበር ዘመቻ በአካባቢው ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ሠራዊቱ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ የተገኘውን ሰላም ለማጽናትና ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራና  ከሰላም ወዳዱ ህዝብም በትብብር እየሰራ መሆኑን ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ ገልጸዋል።

የቄለም ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳደሪ አቶ መንግስቱ ደረሱ በበኩላቸው፤ የዞኑ ሕዝብ ባለፉት አራት ዓመታት የሸኔ የሽብር ቡድን በፈጠረው የጸጥታ ችግር ህዝቡ በሰላም እጦት ሲሰቃይ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ በአካባቢው ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።

በዞኑ የተገኘውን ሰላም ይበልጥ ለማጠናከር የዞኑ ህዝብና አስተዳደር ከሠራዊቱ ጎን በመሆን እየሰራ መሆኑን ምክትል አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም