ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት የሴቶችና የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል

ሀዋሳ፤ ህዳር 17/2016 (ኢዜአ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት የሴቶችና የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በቁርጠኝነት እንደሚደግፍ ተገለፀ።

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ከዓለም ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በሲዳማ ክልል በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ፕሮጀክት ድጋፍ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል ።

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ካንትሪ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ በፕሮጀክቱ አማካይነት የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ናቸው።

በመሆኑም በኢትዮጵያ በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት የወጣቶችንና የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በቁርጠኝነት እንደግፋለን ነው ያሉት ።

በፕሮጀክቱ ለሴቶችና ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን መመልከታቸውን ጠቅሰዋል ።

ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ የአካባቢውን ኢኮኖሚ በማነቃቃትና በክልል ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ዕድገትን፣ ሠላምና መረጋጋትን ጭምር በማምጣት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት እንደ ሀገር የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ መጀመሩን አስታውሰው የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ፕሮጀክት ንቅናቄውን ሙሉ በሙሉ የሚደግፍ ሥራ እንደሚያከናውን ገልፀዋል ።

በዚህም በዶሮ፣ በወተት፣ በዓሣ እና በማር ከ26 ሺህ በላይ መንደሮች ተመስርተዋል ብለዋል።

እነዚህን መንደሮች በዝርያ ማሻሻል የአንድ ቀን ጫጩቶችን፣ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችና ሌሎች ግብዓቶችን በማቅረብ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

አምና 42 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩቶችን ማሰራጨት እንደተቻለ የገለፁት ሚኒስትሩ ዘንድሮ 62 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩቶችን ለማቅረብ አቅደን እየሰራን ነው ብለዋል ።

ዘንድሮ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 9 ሚሊዮን 500 ሺህ ጫጩቶች እንደተሰራጩም ተናግረዋል።

የሌማት ትሩፋትንና መሠል ሀገራዊ ዕቅዶቻችንን በመንግስት በጀት ብቻ ማከናወን አንችልም ያሉት ዶክተር ግርማ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር የሚሰሩ አጋር ድርጅቶች ፕሮግራሞቻቸውን ሀገራዊ ግቡን በሚደግፍ መልኩ እንዲጣጣም እየተደረገ ነው ብለዋል።

በክልሉ በዳሌ ወረዳ ደቡብ መሰንቀላ ቀበሌ የካዮ ሴዮሄ የዶሮ እርባታ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ታዬ ታምሩ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዲግሪ ምሩቅ እንደሆነ ተናግሮ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በዶሮ እርባታ ሥራ መሰማራቱን ገልጿል።

የአንድ ቀን ጫጩቶችን በማስመጣትና አሳድጎ ለገበያ በማቅረብ ውጤታማ ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግሯል።

ለመጀመሪያ ዙር 6 ሺህ 600 የአንድ ቀን ጫጩቶችን አንዱን በ137 ብር በመረከብ ለጥቂት ጊዜያት በመቀለብ 6 ሺህ 367 ጫጩቶችን በ170 ብር ሂሳብ ለተጠቃሚዎች መሸጣቸውን አብራርቷል።

ለወደፊት ሥራቸውን ከዚህም ከፍ በማድረግና እሴት በመጨመር የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚጥሩም ወጣት ታዬ አስረድቷል።

በጉብኝቱ ላይም የግብርና ሚኒስቴር፣ የዓለም ባንክ እንዲሁም የሲዳማ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም