ፍልሰተኞችን ለመቀነስ ሀገራት የስራ ፈጠራን የጋራ አጀንዳ ሊያደርጉት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ፍልሰተኞችን ለመቀነስ ሀገራት የስራ ፈጠራን የጋራ አጀንዳ ሊያደርጉት ይገባል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 17/2016 (ኢዜአ) ፦ እየጨመረ የመጣውን የፍልሰተኞች ቁጥር ለመቀነስ የስራ ፈጠራን ጉዳይ የአለም ሀገራት የጋራ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ20ኛው የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸውም ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የኢንዱሰትሪ አለም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ ቀድሞ ከነበረበት አካሄድ አብዮታዊ ለውጥ ማሳየቱን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በአፍሪካ የሚያጋጥሙ የኢኮኖሚ ስብራቶችና ድህነት የአለም የኢንዱስትሪላይዜሽን ግብን ለማሳካት ማነቆ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአንጻሩ ኢትዮጵያም እ.አ.አ ከ2018 ባካሄደችው የለውጥ ተግባራት ለሁለንተናዊ ብልጽግና አስቻይ እና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመለየት ወደ ተግባር ተገብቶ ዘርፈ ብዙ ለውጥ መመዝገቡን አመልክተዋል።
ህልማችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ያሏትን እምቅ አቅሞች ወደ ተግባር መቀየር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ተቋማትን በመገንባትና ብቁ የሰው ኃይል የማፍራት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሁለገብ ብልጽግናን ለማሳካትም እና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በተሻለ ሁኔታ ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውነናል ብለዋል።
ባለፉት አምስት አመታት በግብርናው ዘርፍ በተካናወኑ አመርቂ ተግባራት በእርሻ የተሸፈነውን መሬት ከ15 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ወደ 22 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዲጂታል ዘርፉም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩን ከማቋቋም ጀምሮ አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል የማሳደግ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ 12 ሰፊ አቅም ያላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ስራ መግባታቸውን አብራርተው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ብቁ ባለሙያ ማፍራትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የስራ ፈጠራ አጀንዳ ዋነኛ የትከረት ጉዳያችን ነው በማለት አስገንዝበዋል።
የስራ ፈጠራ ጉዳይ በዋነኝነት የስደተኞች መዳረሻ የሆኑት አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ሀገራትም የጋራ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ሰፊውን የአፍሪካ የሰው ኃይል በሙያና ብቃት የተሻለ እንዲሆን በማስቻል የስደት ምንጮችን ለመቀነስ አለም አቀፉ ህብረተሰብ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በተለይም በኢንቨስትመንት፣ በፋይናንስና ኢንዱሰትሪ ዘርፍ አካታችና ቀጣይነት ላለው ትብብር በጋራ መስራት እንደሚገባ ነው የገለጹት።