የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት የ24 ሰዓት አገልግሎት መሰጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት የ24 ሰዓት አገልግሎት መሰጠት ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2016(ኢዜአ)፡- የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ከዛሬ ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የ24 ሰዓት ያልተቋረጠ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አብርሆት ቁጥር ሁለት ቤተ መጽሃፍት ለመገንባት ዝግጅቱን ማጠናቀቁም ተገልጿል።
የአብርሆት ቤተ-መጽሕፍት የአገልግሎት የሰዓት ማሻሻያ ማድረጉን አስመልክቶ የቤተ-መጽሐፍቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂኔር ውብአየሁ ማሞ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ቤተ-መጻሕፍቱ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ የዜጎች የማንበብ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በቤተ-መጽሃፍቱ የአንባቢያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተክትሎና የአንባብያንን የሰዓት ማሻሻያ ፍላጎትና ጥያቄ መሰረት አድርጎ 18 ሰዓት የነበረውን አገልግሎት ወደ 24 ሰዓት እንዲያድግ መደረጉን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ቤተ-መጽሃፍትን መገንባት ከተቻለ የአንባቢያን ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን አብርሆት ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።
የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ10 ሚሊዮን የሚልቅ አንባቢ አገልግሎት ያገኘ ሲሆን በቀን ደግሞ 15 ሺህ የሚደርስ አንባቢ እየተገለገለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአንባቢውን ፍላጎት በመረዳትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አብርሆት ቁጥር ሁለት ቤተ መጽሃፍት ለመገንባት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመታት ሊሞላው ነው።