ፌዴሬሽኑ ለክልሎችና ክለቦች ማጠናከሪያ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ማበረታቻ ሽልማት ሰጠ

182

መቀሌ ፤ ህዳር 17/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለክልሎችና ክለቦች አትሌቲክስ እንቅስቃሴ ማጠናከሪያ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ማበረታቻና ሽልማት ሰጠ። 

ፌዴሬሽኑ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል የሁለት ሚሊዮን ብርም ድጋፍ አድርጓል። 

ፌዴሬሽኑ ሽልማቱንና ድጋፉን ያደረገው በመቀሌ ከተማ ባካሄደው 27ኛ ጠቅላለ ጉባዔ ማጠቃለያ ላይ ነው።

ድጋፉ የተሰጠው ስምንት ክለቦች፣ ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በዘርፉ ያደረጉትን እንቅስቃሴ በመገምገም መሆኑ ተመላክቷል።

በዚህም ከፍተኛው 300 ሺህ  ብር፣ ዝቅተኛው ደግሞ 40 ሺህ ብር ለክለቦቹ እና ለክልሎቹ  ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ለክለቦቹና ለክልሎቹ  የማበረታቻ ሽልማትና ድጋፍ የተደረገው አትሌቲክስን ለማስፋፋትና ለማጠናከር የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ መሆኑን ተናግራለች። 

በእያንዳንዱ ክልልና ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የስፖርት አመራሮችና አሰልጣኞች ለዘርፉ ልማት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክሩም አሳስባለች።

የክለቦች፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደር የስፖርት አመራሮችና አሰልጣኞች ፌዴሬሽኑ የሰጣቸውን ድጋፍ የውስጥ አቅማቸው ለማጎልበትና ተተኪ አትሌቶች በፕሮጀክት አቅፈው ለማሰልጠን እንደሚረዳቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ድጋፉን ከረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ተቀብለዋል።

አቶ ጌታቸው ፌዴሬሽኑ ላደረገው ድጋፍ  ምስጋናቸውን በማቅረብ ኢትዮጵያውያን በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም