የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም በሚቀጥሉት አራት ዓመታት 35 በመቶ የገጠሩን ህዝብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል

134

ሆሳዕና  ፤ ህዳር 17/2016 (ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም 35 በመቶ የገጠር ህዝብን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በአማራጭ ሀይል የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተጀምሯል።


 

በመድረኩ መክፈቻ ላይ በሚኒስቴሩ የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር የስራ ሂደት ዋና ሥራ አስፈፃሚ  አቶ ብርሃኑ ወልዱ እንዳሉት፤ የታዳሽ ኃይል አማራጭን በመጠቀም የገጠሩን የሀገሪቱ ክፍል የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በዚህም በሚቀጥሉት አራት ዓመታት 150 ማይክሮ ሀይድሮ ሶላሮች ተገንብተው ለአገልግሎት የሚበቁ ሲሆን ይህም 35 በመቶ የሚሆኑ የገጠር ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

በዚህም እንቅስቃሴ አነስተኛ የሰላር ግሪድ አማራጮችን ጭምር በየአካባቢው እንዲደርስ በማድረግ በተለያየ መንገድ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት መጀመሩን  ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደምም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 10 የሶላር ሚኒ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመተግበር በገጠር የሚኖረውን ማህበረሰብ በመስኖ ልማት፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግና በሌሎች ዘርፎች ተጠቃሚ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ከኤሌክትሪክ አገልግሎት በተጨማሪም ማህበረሰቡ በሌሎች ልማታዊና ተዛማጅ ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳደግ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።

ይህን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አጋር አካላትን በማስተባበር ጠንካራ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የኢነርጂ ባለሙያ አቶ ቢቂላ ታምሩ የታዳሽ ኃይል አማራጭን በማስፋት በክልሉ ገጠር አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለአብነትም በክልሉ ሰበታና ፈንታሌ አካባቢዎች የውሃና የፀሀይ ታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም ኃይል ለማመንጨት በተሰራው ስራ ማህበረሰቡን ከመብራት አገልግሎት በተጨማሪ በሌሎችም ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን  አክለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሀድያ ዞን ግቤ ወረዳ በሚገኘው የለመሬ ተፋሰስን በመጠቀም የማይክሮ ሀይድሮ ፓወር ፕሮጀክት ግንባታ የመስመር ዝርጋታ ስራ ብቻ እንደሚቀረው የተናገሩት ደግሞ በዞኑ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ የኢነርጂ ዘርፍ አስተባባሪ  አቶ ደለለኝ ጌሚሶ ናቸው።


 

ፕሮጀክቱ ከ300 በላይ የአካባቢውን አባወራና እማዎራዎች የኤሌክትሪክና የአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ለ10 ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም