ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እና የአየር ንብረት ለውጥን ያማከሉ ፖሊሲዎች የአፍሪካን ኢኮኖሚ በፍጥነት ለማሳደግ ቁልፍ መንገዶች ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እና የአየር ንብረት ለውጥን ያማከሉ ፖሊሲዎች የአፍሪካን ኢኮኖሚ በፍጥነት ለማሳደግ ቁልፍ መንገዶች ናቸው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2016(ኢዜአ)፡- የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እና የአየር ንብረት ለውጥን ማእከል ያደረጉ የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች የአፍሪካን ምጣኔ ሃብት በፍጥነት ለማሳደግ ቁልፍ መንገዶች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ20ኛው የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
ታሪክ እንደሚያሳየን ኢንዱስትራላይዜሽን በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ከድህነት እንዲወጡ አስችሏል ብለዋል።
በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ሴክተር ሰፊ የስራ ዕድልን በመፍጠር እና የቴክኖሎጂ አቅምን በማሳደግ የሀገራት ብልጽግና ማረጋገጫ ቁልፍ መንገድ ሆኗል ነው ያሉት።
ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የኢንዱስትሪው አለም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ ቀድሞ ከነበረበት አካሄድ አብዮታዊ ለውጥ ማሳየቱን ተናግረዋል።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እና የአየር ንብረት ለውጥን ማእከል ያደረጉ የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች የአፍሪካን ምጣኔ ሃብት በፍጥነት ለማሳደግ ቁልፍ መንገዶች ናቸው ሲሉ ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ የአፍሪካ ሀገራትም ከተቀረው የአለም ክፍል ጋር አካታችና ሁሉን አቀፍ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማሳካት ዝግጁ ናቸው ብለዋል።
አፍሪካ ያላትን ሰፊ አምራች የሰው ሃይል ጨምሮ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ማእድናትን ጨምሮ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች አህጉር መሆኗንም አንስተዋል።
ይህም ለላቀ የኢንዱስትሪ አምራችነትና ኢኮኖሚን ለማሳደግ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን አስረድተው መንግስታት ለአካታችና ሁሉን አቀፍ ብልጽግና በጋራ መስራት ይኖርብናል ብለዋል።