የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2016 (ኢዜአ)፦ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በቴክኖሎጂና የስራ እድል ፈጠራ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
የመግባቢያ ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በተለይም በ'ግድቤ በደጄ' የውሃ ፕሮጀክት ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር እና ቴክኖሎጂውን ለማስፋፋት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢታፋ እና የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ መሰረት በ'ግድቤን በደጄ' ፕሮጀክት የዝናብ ውሃን በማቆር ውሃን ለመጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለመስኖ እና ውሃውን በማጣራት ለመጠጥ ማዋል የሚቻል ይሆናል።
በመጀመሪያ ዙር በ11 ትምህርት ቤቶች በፓይለት ደረጃ የተተገበረ ሲሆን በሁለኛው ዙር በ87 ትምህርት ቤቶች ለማስፋፋት እየተሰራ ይገኛል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢታፋ፤ የፕሮጀክቱ መተግበር በሀገሪቷ ያለውን የውሃ ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ የዝናብ ውሃን በቴክኖሎጂ በመታገዘ መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰው የአገሪቱን የውሃ ሽፋን ለመጨመር ያግዛል ብለዋል።
በትምህርት ቤቶች የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በቀጣይ በሁሉም አገሪቱ አካባቢዎች ለማስፋት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፤ በውሃ ቴክኖሎጂ ላይ ብቁ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር የውሃ ሃብትን የሚያሳድግ በመሆኑ በስምምነቱ መሰረት የሚሰራ መሆኑን ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።