ቀጥታ፡

በማዕድን ሃብት ላይ እሴት በመጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማሳደግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2016 (ኢዜአ)፦በማዕድን ሃብት ላይ እሴት በመጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚያ ልማት ለማዋል  በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ገለጹ።

"የማዕድን ሃብታችን የነገ ተስፋችን" በሚል መሪ ሃሳብ በሚሊኒም አዳራሽ ከኅዳር 14 ጀምሮ እስከ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ለአምስት ቀናት የሚቆየው ኢክስፖ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ቀጥሏል።

በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ እምቅ የማዕድን ጸጋ ጌጣጌጥ እና የከበሩ ማዕድናት ዕሴት መጨመር የሚኖረው ፋይዳ፣  ለማክሮ ኢኮኖሚው ያለው  አስተውጽኦ፣  ተስፋና ተግዳሮቶችን በሚመለከት የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።


 

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቲዮስ፤ የማዕድን ዘርፉ ለአገራዊ የኢኮኖሚ እድገት የራሱን አዎንታዊ ሚና እንዲጫዎት የሚያስችሉ አዳዲስ የአሰራር ሥርዓቶች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በማዕድን ልማት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍትሔ መስጠት የሚያስችል አዲስ የፖሊሲ ማዕቀፍ ተቀርፆ ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ፤ ማክሮ ኢኮኖሚክ በማዕድን ሃብት ልማት ላይ ያለውን መልካም አጋጣሚ እና ተግዳሮት በሚመለከት የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል። 

ማዕድን ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ አቅም ያለው መሆኑን በማብራራት በአፍሪካም ቦትስዋና እና ዛምቢያ እምቅ የማዕድን ሃብታቸውን ለኢኮኖሚ እድገታቸው ማዋላቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያም በማዕድን ሃብት ላይ እሴት በመጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚያ ልማት ለማዋል በልዩ ትኩረት መስራት ይጠበቅባታል ነው ያሉት።


 

የአፍሪካ ማዕድንና ጂኦ-ሳይንስ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኢብራሂም ሻዳድ፤ ማዕድን በአነስተኛ፣ ባህላዊ፣ መካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ የሚለማ ዘርፍ መሆኑን አብራርተዋል።

በመድረኩ የማዕድን አምራቾች፣ ላኪዎች፣ ተጠቃሚዎች፣ የቴክኖሎጂ አልሚና አቅራቢዎች እንዲሁም የአገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።

የማዕድንና ቴክኖሎጅ ኤክስፖ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ መከፈቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም