ቀጥታ፡

የማዕድን ዘርፉን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ለሀገር ልማትና ዕድገት የላቀ አበረክቶ እንዲኖረው መስራት ይግባል- ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2016 (ኢዜአ)፦የማዕድን ዘርፉን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ለሀገር ልማትና ዕድገት የላቀ አበረክቶ እንዲኖረው መስራት ይግባል ሲል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የማዕድን ሚኒስቴርን የ 2016 በጀት የመጀመሪያ ሩብ አመት ሪፖርት ገምግሟል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር በአፈፃፀም ሪፖርቱ ዘርፉ በብልሹ አሰራር፣ ኮንትሮባንድ፣ የጸጥታ ችግርና ህገ ወጥ ትግባራት ዘርፉ እየተፈተነ መሆኑን ገልጿል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ፤ ማዕድን የአገሪቱን ብልጽግና ያረጋግጣሉ ተብለው ከተለዩ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በልማቱ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት ገልጸዋል፡፡



 

ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከልም ብልሹ አሰራር፣ ኮንትሮባንድ፣ የጸጥታ ችግርና ህገ ወጥነት ናቸው ብለዋል። 

በሩብ አመቱ ከማዕድን ዘርፍ 112 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በተጠቀሱት ችግሮች ምክንያት ማሳካት የተቻለው 63 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት በዘርፉ ለ64 ሺህ 471 ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ የተሳካው ለ28 ሺህ 878 ብቻ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል ነው ያሉት።

በዚህም ህገ ወጦችን ተጠያቂ የማድረግ፣ ጥብቅ የቁጥጥር ስርአት መዘርጋት፣ ባለሙያዎችን የማብቃት፣ አሰራሩን ማዘመንና ሌሎችም ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በምክር ቤቱ የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አማርች ባካሎ፤ የማዕድን ዘርፉ በሚፈለገው መጠንና በታቀደው ልክ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ እያበረከተ አይደለም ብለዋል፡፡

በመሆኑም የማዕድን ዘርፉን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ለሀገር ልማትና ዕድገት የላቀ አበርክቶ እንዲኖረው መስራት ይገባል ነው ያሉት።

ለዘርፉ ማነቆ ናቸው ተብለው የተነሱት ህገወጥነት፣ ብልሹ አሰራርና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በጋራና በትብብር መግታት ይገባል ብለዋል።

ለተግባራዊነቱም ቋሚ ኮሚቴው  የሚጠበቅበትን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም