የአየር ንብረት ለውጥንና በሽታን የሚቋቋሙ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረት ለውጥንና በሽታን የሚቋቋሙ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2016 (ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙና ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያስችሉ የቡና ዝርያዎችን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ገለፀ።
በባለሥልጣኑ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ጥበቃ ዴስክ ኃላፊ መኮንን ተሾመ፤ ምርታማነትን የሚጨምሩ በምርምር የተረጋገጡ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የቡና ዝርያዎቹ የቡና ተክል በሽታን ለመቋቋም ትልቅ አቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ አሁን ላይ ከ40 በላይ ምርጥ የቡና ዝርያዎችን በምርምር ለቡና አምራቾች መልቀቃቸውን ጠቁመዋል።
የቡና ዝርያዎቹ በሽታን በመቋቋምና ምርታማነትን በመጨመር ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን ጠቅሰው፤ የቡና አምራቾች የቡና ዝርያዎችን በስፋት እንዲጠቀሙ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ጎን ለጎንም በበሽታ የተያዙትን የቡና ተክሎችን በአግባቡ የማስወገድ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በቡና ተክል ላይ ከሚከሰቱ በሸታዎች መካከል የቡና ፍሬ በሽታ፣ የቡና ግንድ አድርቅ፣ የቡና ቅርንጫፍና ቅጠል ለብላቢና የቡና ሥር አበስብስ በሽታዎች ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል።
የቡና ምርትና ምርታማነትን ከሚቀንሱ የቡና በሽታዎች መካከል ደግሞ የቡና ግንድ አድርቅ በሽታ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ አስረድተዋል።
ለአምራቾችም ዋና ዋና የቡና በሽታዎችን በተመለከተ ግንዛቤ የተፈጠረላቸው በመሆኑም የመከላከሉን ሥራ በአግባቡ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
በሽታ ያጠቃው የቡና ተክል ሲያጋጥም የቡናውን ፍሬ፣ ሥሩንና አጠቃላይ አካሉን በጥንቃቄ በአንድ ቦታ ሰብስቦ የማቃጠል ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል።
በመሆኑም አምራቾች በተለይም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የቡና ተክል በሽታን የመከላከል ሥራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህን ተግባራት ማጠናከር እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።
ቡና በተነቀለበት ቦታ እስከ ሁለት ዓመት ሌላ ቡና መልሶ አለመትከልም ይገባል ሲሉም ገልፀዋል።
በተለይም የቡና ፍሬ በሽታ የታየበት የቡና ተክል በዕይታ የሚለይ በመሆኑ፤ እየተካሄደ ባለው የእሸት ቡና ምርት ስብሰባ ተቀላቅሎ እንዳይገባ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።
የቡና በሽታን ለመከላከል የኬሚካል ርጭት በቡና ጣዕም ላይ ተጽዕኖ ስለሚያመጣ፤ የቡና ማሳን በአግባቡ በማረም፣ በመመቀስ (ቅርንጫፍ በማሳሳት)፣ ሽበት በማራገፍና በአጠቃላይ ንጹህ በማድረግ በሽታን መከላከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።