ወለጋ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የተመደቡለትን ተማሪዎች በመቀበል ላይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወለጋ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የተመደቡለትን ተማሪዎች በመቀበል ላይ ነው
ነቀምቴ ፤ ህዳር 17/2016 (ኢዜአ) ፦ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በ2016 የትምህርት ዘመን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች አዲስ የተመደቡ 2 ሺህ 700 ተማሪዎችን በመቀበል ላይ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ነቀምቴ ከሚገኘው ዋናው ግቢ በተጨማሪ በግምቢ እና ሻምቡ ካምፓሶቹም የሚያስተምራቸውን ተማሪዎች እየተቀበለ ነው።
የወለጋ ዩኒቨርስቲ የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ከበደ ነሞምሳ፣ ለተማሪዎቹ ''የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በማለፍ ለከፍተኛ ትምህርት በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ'' ብለዋል።
ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው በሚኖራቸው ቆይታ የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት መትጋት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበው፤ ትኩረታቸውንም ትምህርት ላይ ብቻ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ዩኒቨርስቲው በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 2ሺህ 700 አዲስ ተማሪዎችን በሶስቱም ካምፓሶቹ ተቀብሎ እንደሚያስተምር ገልጸው፤ የትምህርት ጥራት የማስጠበቁ ስራም በልዩ ትኩረት ይከናወናል ብለዋል።
የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ተወካይ አቶ አሸናፊ ከበደ በበኩላቸው የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ ለተማሪዎቹ ቤተሰብ ሆኖ እንደሚንከባከባቸው ተናግረው፤ ተማሪዎቹም በተረጋጋ መንፈስ ትምህርታቸውን መከታተል እንዳለባቸው አመልክተዋል።
አዲስ ተመድበው ወደ ዩኒቨርሲቲው እየገቡ ካሉ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ዮሐንስ ኩመራ እንዳለው በነባር ተማሪዎችና በመምህራን የተሰጣቸውን ምክር በመቀበል ትኩረቱን ትምህርት ላይ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጿል።
ተማሪ ተሊሌ ተስፋዬም በበኩሏ በካምፓስ በሚኖረኝ ቆይታ ያለኝን ሰዓት በአግባቡ ተጠቅሜ በመማር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አቅጄያለሁ ብላለች።