ቀጥታ፡

ፀረ ሠላም ኃይሎች ለመከላከያ ሠራዊቱ እጃቸውን በሠላም እየሰጡ ነው

 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2016 (ኢዜአ)፦ ሰሞኑን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ የነበረው ፀረ ሠላም ኃይል በሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል እየተወሰደበት ባለው ጠንካራ እርምጃ በሠላም እጁን እየሰጠ ይገኛል።

በቦታው ተገኝተው የሠራዊቱን የግዳጅ አፈፃፀም የተመለከቱት የሰሜን ሸዋ ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጄኔራል አበባው ሠይድ "እናንተ ፀረ ሠላም ኃይሎች የተሰጣችሁን እድል በመጠቀም ቆም ብላችሁ በመገንዘብ ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት እጃችሁን በሠላም ስለሰጣችሁና ወደ ሠላም በመምጣታችሁ ለሀገራችን የጋራ እድገት የሚጠቅም ነው" ብለዋል።


 

ኮሎኔል ግርማ ደምለው በበኩላቸው በሠላም እጅ መስጠት ለሀገርም ለክልሉም የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልፀው፤ በቀጠናው የተሰማራው የሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል የሕዝብና የመግሥትን ፍላጎት ለማሳካት ብሎም ዘላቂ ሠላም ለማምጣት በትጋት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ሠራዊቱ የተሰጠውን ሀገራዊ ግዳጅ ጥንቃቄ በተሞላበት አግባብ የሕዝብን ሠላም ባረጋገጠ ሁኔታ እየተወጣ እንደሚገኝም ኮሎኔል ግርማ መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም