የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በቀን 10 ሺህ ቶን ክሊንከር ሲሚንቶ ማምረቻ ግንባታ ከ4 ወር በኋላ ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በቀን 10 ሺህ ቶን ክሊንከር ሲሚንቶ ማምረቻ ግንባታ ከ4 ወር በኋላ ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል
አዲስ አበባ ፤ህዳር 16/2016 (ኢዜአ)፦የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በቀን 10 ሺህ ቶን ክሊንከር ሲሚንቶ ማምረቻ የኪልን እና የቅድመ ማሞቂያ መሳሪያዎች ተከላ ከአራት ወራት በኋላ ተጠናቆ ማምረት እንደሚጀምር ተገለጸ።
የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በ600 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሰባት የሚደርሱ የግንባታ መሳሪያዎችን ለማምረት የተቋቋመ ግዙፍ ፋብሪካ ነው፡፡
የኢስት አፍሪካ ሆልዲን እና ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ሊቀመንበር ብዙአየሁ ታደለ፣ የግንባታ ሂደቱ በመጠናቀቅ ላይ ያለው የሲሚንቶ ፋብሪካ በአፍሪካ ግዙፉ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
የፋብሪካውን ግንባታ በ18 ወራት ለማጠናቀቅ በተያዘለት እቅድ መሰረት በ11 ወራት ውስጥ መሰረታዊ የሚባሉት የግንባታ ሂደቶች በፍጥነትና በጥራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ የኪልን እና የቅድመ ማሞቂያ መሳሪያዎች ተከላ የተጠናቀቀለት ፕሮጀክት በቀን 10 ሺህ ቶን ክሊንከር ሲሚንቶ የማምረት አቅም አለው ብለዋል፡፡
በቀን 10 ሺህ ቶን ክሊንከር ሲሚንቶ ማምረቻ የኪልን እና የቅድመ ማሞቂያ መሳሪያዎች ተከላ ተጠናቆ ከአራት ወር በኋላ በመጋቢት ወር ማምረት ይጀምራል ብለዋል፡፡
የዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲግ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ዋንግ ፋይን፤ የፋብሪካው ግንባታ በተያዘለት ጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ግንባታው ያለ ምንም የጸጥታ ችግር በጥራትና በፍጥነት እንዲከናወን የአካባቢው ህዝብና መንግስት አበርክቶ የጎላ እንደነበር አንስተዋል፡፡
የናሽናል ሲሚንቶ ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሊዩ ጂያንጁን፤ ይህ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የሲሚንቶ ፋብሪካ የኢትዮጵያ ግዙፉ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኩራት የሆነው ይሄው ፕሮጀክት 10 ሺህ ቶን ክሊንከር ማምረት የሚችልበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡
የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አበባው በቀለ፤ ፋብሪካው በአፍሪካ ግዙፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቅድመ ማቀጣጠያ ዩኒቱ ከፍታው 147 ሜትር መሆኑን ገልጸው፤ ይሄም በዓለም ትልቁ ያደርገዋል ነው ያሉት።
የምዕራፈ ቅዱሳን በልበልቲ ኢየሱስ አንድነት ገዳም ዋና አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ሀረገወይን አድማሱ፤ መንግስት ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል።
በመሆኑ የፋብሪካውን የሥራ እንቅስቃሴ በቅርበት በመከታተል በባለቤትነት የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።