በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 60 በመቶ በጥምር ግብርና የለሙ ናቸው--ዶክተር ግርማ አመንቴ

ሀዋሳ ፤ህዳር 16/2016 (ኢዜአ)፦ በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉ ችግኞች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት በጥምር ግብርና የለሙ መሆናቸውን የግብርና ሚንስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ።

ህብረተሰቡ ለተተከሉ ችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። 

ሚኒስትሩ ባለፈው የክረምት ወቅት በሲዳማ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተተከሉ ችግኞች እየተደረገ ያለውን የእንክብካቤ ሥራ ዛሬ በመስክ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ዶክተር ግርማ ለኢዜአ እንዳሉት፤  በመንግስት አቅጣጫ መሠረት በሁለተኛው ምዕራፍ ከሚተከሉ ችግኞች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት በጥምር ግብርና እንዲለሙ ተደርጓል።

በእዚህም ፍራፍሬና የእንስሳት መኖን በጥምር ለማልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

ከሚተከሉ ችግኞች 60 በመቶውን በጥምር ግብርና እንዲለማ የተደረገበት ምክንያት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ ታስቦ መሆኑንም አስረድተዋል።

ቀሪዎቹ የተተከሉ ችግኞች ለደን ልማትና ለከተማ ውበት የሚያገለግሉ መሆናቸውንም ዶክተር ግርማ ገልጸዋል።

“በክረምቱ ለተተከሉ ችግኞች በህዝብ ተሳትፎ እየተደረገ ባለ የእንክብካቤ ሥራ የተሻለ የጽድቀት መጠን ላይ ይገኛሉ” ብለዋል።

"የጥምር ግብርና በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የሚሰራና አርሶ አደሩም ጥቅሙን እስካየ ድረስ በየቀኑ የማረም፣ ውሃ የማጠጣትና የመንከባከብ ሥራ ስለሚሰራ የጽድቀት መጠኑ ከፍ ይላል" ብለዋል።

በዚህ ረገድ በሲዳማ ክልልም ሆነ እንደአገር የተሰራው ሥራ መልካም መሆኑን ጠቅሰው፤ በበጋ ወራትም የችግኝ እንክብካቤ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።  


 

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ  በአረንጓዴ አሻራ የተያዘውን መርሃ ግብር ለማሳካት እየሰራ ነው።

በክልሉ ባለፈው ዓመት ብቻ ስነ ምህዳርን መሠረት ባደረገ መልኩ 306 ሚሊዮን የተለያየ ጥቅም የሚሰጡ ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመዋል።

የጥምር ግብርና ልማትን ለማሳካት ለቡና፣ ፍራፍሬ እና እንስሳት መኖ ልማት ትኩረት መሰጠቱንም አስታውሰዋል።

በክልሉ የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠን በአማካይ ከ85 በመቶ በላይ መሆኑን ገልጸው፣ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለችግኞች የሚደረገው የእንክብካቤ ሥራ ቀጣይ እንደሚሆን አመልክተዋል።


 

በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ የሞርቾ ነጋሽ ቀበሌ አርሶ አደር ጦና ጦምራ በሰጡት አስተያየት ስልጠና ወስደው የጥምር ግብርና ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ባላቸው አነስተኛ መሬት ላይ የተሻሻሉ የአቮካዶ ችግኞችን ከቡናና እንሰት ጋር አቀናጅተው ማልማታቸውን ገልጸዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ካለሙት አቦካዶ 25 ኩንታል ለይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ በማቅረብ 87 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ 580 የአቮካዶ ችግኞችን በመትከል እየተንከባከቡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም