ቀጥታ፡

​​​​​​​በአካባቢያችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ሆነን እንሰራለን - የአንኮበር ወረዳ ነዋሪዎች

ደብረ ብርሃን ፤ ህዳር 16/2016 (ኢዜአ)፦በአካባቢያቸው የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ሆነው በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ በሰሜን ሸዋ ዞን የአንኮበር ወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ።

በወረዳው አልዩ አምባ ከተማ ነዋሪዎች በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።

የከተማው ነዋሪ አቶ ተፈሪ ተስፋየ እንደገለጹት፤ በአካቢያቸው ባለፉት ሁለት ወራት ተከስቶ በነበረው የሰላም እጦት በኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ጉዳት ደርሷል።

የፀጥታ ሃይሉ ባደረገው ያልተቋረጠ እንቅስቃሴ በአካባቢያቸው ሰላማዊ ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅትም የሰላምና መረጋጋት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል።

እርሳቸው የተሟላ ሰላም ለማምጣት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ወጣቶችን ስለ ሰላምና አንድነት ከማስተማር ባለፈ አጥፊዎችን በማጋለጥ ለዘላቂ ሰላም መስፈን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ሌላው ነዋሪ አቶ አሊዩ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ችግሮችን በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች ሲፈቱ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ አሁንም የሚስተዋሉ የሰላም እጦት ችግሮችን ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት እንደሚያግዙ ጠቁመዋል።

በተለይም ሳያውቁ በስህተት ለሰላሙ መታጣት ምክንያት የሆኑ ወጣቶችን በመምከር ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

"በአካባቢው የጥፋት ቡድኑ አባላት እየፈፀሙት ባለው ችግር በመንግስትና በህዝብ ንብረት ላይ የከፋ በደል አድርሷል'' ያሉት ደግሞ የአንኮበር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታደስ ፈቅ ይበሉ ናቸው።

የፀጥታ መደፍረስ ችግሩን በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት በተደረገ ጥረት በአካባቢው ሰላም ማስፈን መቻሉን ጠቁመው፤ "የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ አሁንም ሥራዎች እየተሰሩ ነው" ብለዋል።

የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አባል እና የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ተከስቶ የነበረውን የሰላም መታጣት ችግር ለመቀልበስ በተሰራው ሥራ በዞኑ የተሻለ ሰላም ማስፈን ተችሏል።

የፀጥታ ሐይሉ ከሰላም ወዳዱ ህዝብ ጋር በቅንጅት ባከናወነው ሥራ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ህዝቡ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።


 

የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢና የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል አበባው ሰይድ እንደገለፁት፤ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም መላ ህዝቡ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ መስራት አለበት።

የአገር መከላከያ ሠራዊቱ ህዝቡን በማስተባበር አጥፊዎችን ከህዝብ የመለየትና ሰላም የማስከበር ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

በተሳሳተ መንገድ ከፅንፈኛ ቡድኑ ጎን ተሰልፈው የነበሩ አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር በማዋልና ተገቢውን የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉንም ተናግረዋል።

አሁንም ሰላም የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ በተሳሳተ አመለካከት በጫካ ያሉ ወጣቶችም ወደ ሰላም እንዲመለሱና ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲመሩ አሳስበዋል።

በውይይት መድረኩ በየደረጃው ያሉ አመራር አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም