በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አራት የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓለም አቀፍ የጥራት ተቀባይነት አገኙ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2016 (ኢዜአ)፦በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ስር የሚገኙ አራት የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓለም አቀፍ የጥራት ተቀባይነት አገኙ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ዩኒቨርሲቲው ባለፋት 60 አመታት ዕውቅ ምሁራን ከማፍራት በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን መስራቱንና አሁንም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በዩኒቨርሲቲው ቴክኖለጂ ኢንስቲቲዩት ስር የሚገኙ አራት የትምህርት ዘርፎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥራት ተቀባይነት ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል። 

የኤሌክትሪካል፣ መካኒካል፣ የሲቪልና ኬሚካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍሎችም እውቅናው የተሰጣቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዕውቅናው ABET በተባለ አለም አቀፍ ድርጅት መሰጠቱን በመጥቀስ ይህም አለም አቀፍ መምህራንና ተማሪዎች ለመቀበል እድል ይፈጥራል ብለዋል።

የተገኘው ዕውቅና በኢኒስቲቲዩቱ የሚሰጡ ስልጠናዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያግዛል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ዕውቅናውን ለማግኘት ላለፋት አራት አመታት ሰፋፊ ስራዎች  ሲያከናውን መቆየቱንም አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው የተማሪዎች ምረቃ ሥነሥርዓት ላይ  ለጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የክብር ዶክትሬት ሽልማት መስጠቱም ይታወሳል።

በዚሁ መሰረትም በዛሬው እለት በአዲስ አበባ በተከናወነ ስነ ስርአት ላይ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ከዩኒቨርሲቲው የተሰጣትን የክብር ዶክትሬት ተረክባለች።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም