የአበበች ጎበና በጎ አድራጎት ድርጅት በማርሻል አርት ስፖርት ያሰለጠናቸውን ወጣቶችና ታዳጊዎች አስመረቀ

303

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2016 (ኢዜአ)፦የአበበች ጎበና በጎ አድራጎት ድርጅት ለሁለት ዓመታት በማርሻል አርት ስፖርት ያሰለጠናቸውን 32 ወጣቶችና ታዳጊዎች አስመረቀ።

የታዳጊዎችና ወጣቶቹ ስልጠና ድርጅቱ ባመቻቸው በጎ ፈቃደኛ የማርሻል አርት ባለሙያ የተከናወነ ሲሆን ስልጠናውን አጠናቀው በዛሬው እለት ለምርቃት በቅተዋል።

ተመራቂዎቹ በስልጠናው የአካል ብቃትና የስነ ልቦና ዝግጁነት እንዲኖራቸው በማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ድንቁ ረጋሳ፣ ነብዩ ዳንኤል እና ቅድስት ረጋሳ የስልጠናው እድል ስለተመቻቸላቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይ በዚህ ስፖርት ተሻለ ደረጃ ለመድረስ እንደሚሰሩና ሌሎች ወጣቶችንም ለማሰልጠን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በአበበች ጎበና በጎ አድራጎት ድርጅት የማርሻል አርት ስፖርትን በበጎ ፈቃደኝነት እያሰለጠነ የሚገኘው ኢንትርናሽናል ኢንስትራክተር አብዱልቃድር ረጌሶ፤ ስፖርቱ በተለይ ለወጣቶችና ታዳጊዎች በብዙ መልኩ ጠቃሚ መሆኑን አስረድቷል።


የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶችን በሥነልቦና፤ በአካል ብቃትና በራስ መተማመን እንዲያድጉ ለማድረግ የድርሻውን አስተዋጽኦ በማድረጉ ደስተኛ መሆኑንም ገልጿል።

በድርጅቱ የልጆች መምሪያ ጉዳይ ኃላፊ ወይንሸት ዳምጠው፤ ድርጅቱ ታዳጊ ህፃናትና ወጣቶችን ከማሳደግና ከማስተማር ባለፈ ስፖርታዊ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ እንደነበር ገልፀዋል።

በቀጣይም እንዲህ ዓይነቱ ስፖርት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው የዛሬ ተመራቂዎችም የማርሻል አርት ስፖርትን በማሳደግ የደርሻቸውን እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።

የአበበች ጎበና በጎ አድራጎት ድርጅት በ1972 ዓ.ም በክብር ዶክተር አበበች ጎበና አማካኝነት የተመሰረተ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም