የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን  ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ

መቀሌ፤ ህዳር 16/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 27ኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2016 ዓመት ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በማፅደቅ ተጠናቀቀ።

ፌዴሬሽኑ ላለፉት ሁለት ቀናት ባካሄደው ጉባኤው ያጸደቀው በጀት ለስልጠና እንዲሁም ለስፖርታዊ ውድድሮች ማካሄጃ ጭምር የሚውል መሆኑ ተመላክቷል።

በዚህም ለወጣቶች የፕሮጀክት ስልጠና ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የጉባኤው ተሳታፊዎች ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ “ሃገራችንን በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያን ይበልጥ ከፍ ለማድረግና የዘርፉን የገቢ ምንጭነት ለማሳደግ ከክልሎች ፌዴሬሽኖች ጋር በተቀናጀ አግባብ እንሰራለን “ ብላለች።


 

በጉባኤው መዝጊያ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠብቀውን ውጤት የሚያመጡ አትሌቶችን በብዛት ለማፍራት ክልሎች ከፌዴራል ጋር ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ስፖርት ለአገር ሰላምና ፍቅር እንዲሁም አንድነትና ልማት መረጋገጥ ዓይነተኛ መሳሪያ በመሆኑ አሰልጣኞችና አመራሮች ለተግባራዊነቱ ግንባር ቀደም ሊሆኑ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በተጨማሪም ለበጀት አጠቃቀምና ለስፖርት ስነ ምግባር ትኩረት መሰጠቱን አምባሳደር መስፍን አስታውቀዋል ።

በጉባኤው የተሳተፉት የክልሎች አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች አመራሮች በበኩላቸው በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የሚያግዝ የወዳጅነት ውድድር ለማካሔድና ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በጉባኤው የሁሉም ክልሎች የስፖርት አመራሮችና አስልጣኞች ተሳትፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም