ቀጥታ፡

የሙስና ወንጀልን በመከላከል ሂደት 9 ቢሊየን ብርና ከ4 ሚሊየን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ማስመለስ ተችሏል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 16/2016 (ኢዜአ)፦ የሙስና ወንጀልን በመከላከል ሂደት 9 ቢሊየን ብርና ከ4 ሚሊየን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ማስመለስ መቻሉን የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት መንግስት ሊሰራቸው ካቀዳቸው ተግባራት መካከል ሙስናንና ብልሹ አሰራርን መከላከል ቀዳሚው ነው፡፡

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 25 ቀን 2016 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲከፈት ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት ሙስናን ለመከላከል ትልቅ ትኩረት መስጠቱን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተቋቋመው የሙስና መከላከል ግብረ ኃይል አሁን ላይ ተጨባጭ ለውጥ ያሳዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን የፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው፤ ኮሚሽኑ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ተጋላጭ ዘርፎችን በመለየት በርካታ ተግባራት አከናውኗል ብለዋል።

በዚህም ኮሚሽኑ በዋናነት ለሙስናና ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎችን ለመለየት ባደረገው ጥናት የመሬት፣ የግዥና ንብረት እንዲሁም የኮንትራት አስተዳደሮችና የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ለሙስና ተጋላጭ መሆናቸውን ለይቷል ብለዋል። 

ይህን ተከትሎ የተቋማትን የሙስና ተጋላጭነት በማጥናትና ለሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተደራሽ በማድረግ ብልሹ አሰራርንና ሌብነትን ለማስቀረት ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ በዋናነት ሙስናን ለመከላከል በቅንጅት ባከናወናቸው ተግባራት 9 ቢሊየን የሚጠጋ ጥሬ ብርና ከ4 ሚሊየን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡


 

በፌደራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ስልጠና መሪ ስራ አስፈጻሚ ዳግም አላምረው፤ ኮሚሽኑ የሙስና ተግባራትን ለመከላከል ከፌደራል ፖሊስና ከፍትህ ሚኒስትር ጋር በመቀናጀት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም የመሬት፣ የግዥ ስርአትና የኮንትራት አስተዳደር የሙስና ተጋላጭነት ከፍተኛ በመሆኑ ኮሚሽኑ ትኩረት በመስጠት እየሰራባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከማህበረሰቡ የሚደርሱትን ጥቆማዎች ከመረመረ በኋላ ለሁለቱ ተቋማት በማስተላለፍ በርካታ የመንግስት ሃብት ከብዝበዛ መታደግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ሙስናን የመከላከል ተግባር ለአንድ ወገን የሚተው ስራ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ ከኮሚሽኑ ጎም በመቆም ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ምክትል ኮሚሽነሩ እሸቴ አስፋው ጠይቀዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም