የተቋማትን ምርትና አገልግሎት ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ ከተወዳዳሪነት ባለፈ ለሀገር እድገት እንዲሰሩ ማድረግ ይገባል- ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2016 (ኢዜአ)፦ የተቋማትን ምርትና አገልግሎት ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ ከተወዳዳሪነት ባለፈ ለሀገር እድገት እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ያዘጋጀው 10ኛው ዙር አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በትላንትናው እለት ተካሂዷል። 

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ በጥራት ውድድሩ ከሽልማት ባለፈ ተቋማት የተሞከሮ ልውውጥ እንዲያደረጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን ቀልጣፋና ዘመናዊ በማድረግ ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በቀጣይም ተቋማት የምርትና አገልግሎት ጥራትን በማረጋገጥ ለአገሪቱ እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።  


 

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት፤ በአምራች፣ በአገልግሎት፣ በጤና እና በትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት በውድድሩ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በተቀመጠው እስታንዳርድ መሰረትም 38 ተቋማት በየደረጃው ሽልማት መውሰዳቸውን ጠቅሰው በቀጣይም አሰራራቸውን ይበልጥ በማዘመን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

ከተሸላሚዎቹ መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የተቋማት ተወካዮች በተሰጣቸው እውቅና መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይ ለተሻለ ምርትና አገልግሎት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም