ተቋማት ጥራትን የሥራቸው ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል - ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማት ጥራትን የሥራቸው ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል - ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 15/2016 (ኢዜአ) ፦ተቋማት ጥራትን የሥራቸው ማዕከል አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ያዘጋጀው የ10ኛው ዙር አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ማምሻውን በቤተ-መንግሥት ተካሂዷል።
በውደድሩ የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ 38 ተቋማት ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
በመርኃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንትና የድርጅቱ የበላይ ጠባቂ ሣህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ፤ ተቋማት ጥራትን የሥራቸው ማዕከል አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ተቋማት ከተቀመጠ ስታንዳርድ ጋር ውድድር በማድረግ የምርትና የአገልግሎታቸውን ጥራት ለማስጠበቅ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዛሬ ለሽልማት የበቁ ተቋማት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው፤ በየዓመቱ የሚያከናወነው ሽልማት ተቋማትን አቅማቸውን ለማጎልበት ያለመ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ተቋማት በውድድር ሂደቱ ተሞክሮዎች፣ የሚሰጣቸውን ጠቃሚ አስተያየቶች የእቅዶቻቸው አካል በማድረግና ተቋማዊ አሰራሮችን በማስፈን ዘመን ተሻጋሪ መለያ ለመፍጠር መትጋት አለባችሁ ብለዋል።
በተጓዳኝም፤ ያሏችሁን ጥንካሬዎች በማስቀጠል እንዲሁም ማስተካከል የሚገባውን በማረም በቀጣይም ተቋማት የምርትና አገልግሎት ጥራትን በማረጋገጥ ለአገሪቱ እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በዘንድሮ የአገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ውድድር በርካታ የመንግሥት ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሰው ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኮንሰትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው፤ በኮንሰትራክሽን ዘርፍ የሚነሱ የጥራት ችግሮችን ለማቃለል እየተሰራ ነው ብለዋል።
ጎን ለጎንም በዘርፉ የግብዓት እጥረት እንዳይከሰት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን የኮንስትራክሽን ግብዓት አቅርቦት ተደራሽነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጥራትን የማረጋገጥ ጉዳይ የአንድ ተቋም ብቻ አለመሆኑን ጠቁመው ሁሉም አካላት ይህንን እውን ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት አምራቾችን፣ አገልግሎት ሰጪዎችና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ድርጅቶችን በማወዳደር እውቅናና ሽልማት ይሰጣል።