በአኝዋሃ ብሔረሰብ ዞን ያለውን የተፈጥሮ ደን በባዮስፌር ሪዘርቭነት ለማስመዝገብ የሚያስችል ጥናት ተጠናቀቀ

ጋምቤላ፤ ህዳር 15/2016(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል በአኝዋሃ ብሔረሰብ ዞን ያለውን የተፈጥሮ ደን በባዮስፌር ሪዘርቭነት ለማስመዝገብ የሚያስችል ጥናት መጠናቀቁን የክልሉ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ አስታወቀ።

ደኑን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት( ዩኔስኮ) በባዮስፌር ሪዘርቭነት ለማስመዝገብ በተካሄደው ጥናት ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ  ተካሄዷል። 


 

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ መሠረት ማቲዎስ በምክክር መድረኩ ላይ እንዳሉት፤ የአኝዋሃ ብሔረሰብ ዞን በተፈጥሮ ሃብት የበለፀገ አካባቢ ነው ብለዋል። 

ይህንን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት( ዩኔስኮ) በባዮስፌር ሪዘርቭነት ለማስመዝገብ ጥናት መጠናቀቁን ተናግረዋል። 

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ለተጀመረው ጥረት መሳካት በዞኑ ያለውን የተፈጥሮ ደን ማስመዝገብ ጠቀሜታው ጉልህ መሆኑን አብራርተዋል ።


 

ቢሮው የተፈጥሮ ደኑ በድርጅቱ እንዲመዘገብ ለሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ  ኃላፊዋ አረጋግጠዋል። 

የአኝዋሃ ባዮስፌር ሪዘርቭ አጥኚ ድርጅት አማካሪ ፕሮፌሰር ቂጤሳ ሁንዴራ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የአኝዋሃ ዞን የተፈጥሮ ደን በብዝሃ ሃብቱ እጅግ የበለፀገ ነው ብለዋል። 


 

ሃብቱ በድርጅቱ ቢመዘገብ ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ሀብት ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ከማድረግ ባለፈ፤ የጥናትና የምርምር ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ያስችላል ብለዋል።

የአኝዋሃ ባዮስፌር ሪዘርቭ አማካሪ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቶሌራ አብርሃም በበኩላቸው ደኑን በድርጅቱ እንዲመዘገብ የሚያደርግ  ብዝሃ ህይወት ያለበት አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

በተለይም አካባቢው ከአንድ ሺህ የሚበልጡ የእፅዋትና የተለያዩ እንስሳት ዝርያዎችን በውስጡ አምቆ የያዘ የተፈጥሮ ሃብት መሆኑን ተናግረዋል። 

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሰው ልጅ አኗኗር ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ የተፈጥሮ ሃብቱን በመጠበቅና በመንከባከቡ ረገድ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ  ወሳኝ ነው ብለዋል። 

ጥናቱ የተካሄደው ''መልካ ኢትዮጵያ'' የተባለ ሃገር በቀል ድርጅት ከአኝዋሃ ዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር መሆኑም ተመላክቷል። 

ድርጅቱ የማጃንግ የተፈጥሮ ደንን በማጥናት በባዮስፌር ሪዘርቭነት እንዲመዘገብ ማድረጉ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም