የኢትዮጵያን ክብርና መልካም ገፅታ የሚያጎሉ አትሌቶች እንዲበራከቱ የሚደረገው ጥረት መጠናከር አለበት-አቶ ጌታቸው ረዳ

704

መቀሌ ፤ ህዳር 15/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ክብርና መልካም ገፅታ ከፍ የሚያደርጉ እውቅ አትሌቶችን የማበራከቱ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፈዴሬሽን 27ኛ መደበኛ ጉባዔ በመቀሌ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።


 

አቶ ጌታቸው በጉባዔው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የኢትዮጵያን መልካም ገፅታና ክብር ከፍ የሚያደርጉ እውቅ አትሌቶች እንዲበራከቱ የሚደረገው እንቅስቃሴ መጎልበት አለበት።

ክልሎች "ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባናል" ብለዋል።

ለዚህም በክልሎች አትሌቶች በብዛት የሚያፈሩ የአትሌቲክስ መንደሮችን መገንባትና አስልጣኞችን ማፍራት ወሳኝነት እንዳለው አመልክተዋል።

በክልሉ ስለ ስፖርትና ልማት ማውራት መጀመሩ ትልቅ እመርታ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፤ ስፖርት የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና ልማት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ለስፖርት ልዩ ትኩረት በመስጠት የኢትዮጵያ አምባሳደሮች የሚሆኑ ወጣት አትሌቶችን ማፍራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፤ ክልሎች ከፌዴሬሽኑ ጋር ተቀናጅተው ወጣቶች ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ይዘው እንዲቀረፁና ለስፖርቱ እድገት ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ ጠይቃለች።

እስከ ነገ የሚቆየው ጉባዔ በ2015 በጀት ዓመት ሥራ አፈፃፀምና በ2016 በጀት ዓመት እቅድና በጀት ላይ በመወያየት ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም