ቀጥታ፡

በፈረንሳይ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ውድድር የተቋቋመው የቅድመ ዝግጅት የቴክኒክ ኮሚቴ ወደ ሥራ ሊገባ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 15/2016 (ኢዜአ) ፦  በፈረንሳይ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ውድድር የተቋቋመው የቅድመ ዝግጅት የቴክኒክ ኮሚቴ ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1956 በአውስትራሊያ ሜልቦርን ከተማ በተካሄደው ኦሊምፒክ መጀመሩ ይታወሳል።

በወቅቱም ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ በቦክስና በብስክሌት የውድድር ዓይነት እንደተሳተፈች የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1960፤ አበበ ቢቂላ በማራቶን ውድድር ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ ካመጣበት ኦሊምፒክ ጀምሮ፤ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ውጤታማ ተሳትፎ ስታደርግ ቆይታለች።

ከአራት ዓመታት በፊት ጃፓን ላይ በተደረገው ኦሊምፒክ በሰሎሞን ባረጋ አማካኝነት በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣችበት ውጤት ደግሞ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

በቀጣይ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2024 በፈረንሳይ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ በአትሌቲክስና በውሃ ዋና ትሳተፋለች።

በአትሌቲክስ ውድድርም ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ባሉት ርቀቶች እንደምትሳተፍ ታውቋል።

በቀጣይም በብስክሌት፣ በቴኳንዶና በጁዶ የሚወዳደሩ ስፖርተኞች በኦሊምፒኩ የሚያሳትፋቸውን ውጤት ካስመዘገቡ፤ ኢትዮጵያ በሌሎች የስፖርት ዓይነቶችም እንደምትሳተፍ የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የፓሪስ ኦሊምፒክ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቢልልኝ መቆያ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በፈረንሳይ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ውድድር ቅድመ ዝግጅት የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሯል።

ኮሚቴው ከኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን በማዘጋጀት የአትሌቶች ምዝገባ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶቹ ከፓሪስ ሞቃታማ አየር ጋር የሚቀራረብ ሥፍራ ላይ ልምምድ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።

የአትሌቶች የዝግጅት ጊዜን በተመለከተ ደግሞ ለውድድሩ አራት ወር ሲቀረው ኦሊምፒክ ኮሚቴው በሚመርጠው ሆቴል የመጨረሻ ዝግጅታቸውን እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም