የጋምቤላ ክልልን የግብርና ልማት በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ድጋፍ እያደረኩ ነው-ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ክልልን የግብርና ልማት በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ድጋፍ እያደረኩ ነው-ኢንስቲትዩቱ
ጋምቤላ ፤ ህዳር 15/2016 (ኢዜአ) ፦በጋምቤላ ክልል የግብርና ልማት በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ለክልሉ ሥነ ምህዳር ተስማሚ የሰብልና የእንስሳት ቴክኖሎጂዎችን እያላመደና እያስተዋወቀ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ድሪባ ገለቲ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የክልሉ የግብርናውን ልማት ለማዘመን የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረገ ነው።
በክልሉ የሚተገበረውን የ10 ዓመት የግብርና ሽግግር ፕሮግራም ስኬታማ ለማድረግ ከክልሉ ግብርና ምርምር ተቋም ጋር በመቀናጀት አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅና የማላመድ ሥራዎችን እንደሚያከናውን አስረድተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በአቦቦ ግብርና ምርምር ማዕከል ለአካባቢው ሥነ- ምህዳር ተስማሚነት ያላቸውን የስንዴ፣ የበቆሎ፣ የማሽላ፣ የአኩሪ አተር፣ የእንስሳት መኖና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመለየት እያስተዋወቀ መሆኑንም ተናግረዋል።
በቀጣይም በፍራፍሬ፣በሰብልና በጓሮ አትክልት ላይ አትኩሮ እንደሚሰራም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
በስንዴ የተገኙት አራት ዝርያዎች በሄክታር ከ38 እስከ 40 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ሲሆን፣ በአኩሪ አተር የተገኙት ሦስት ዝርያዎች ደግሞ ከ35 እስከ 40 ኩንታል ምርት ማስገኘት ይችላሉ ብለዋል።
እንዲሁም በበቆሎ በሄክታር እስከ 80 ኩንታል የሚያስገኘው ዝርያ በክልሉ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች እጅ ከሚገኙት ዝርያዎች በእጥፍ ብልጫ ያለው ምርት እንደሚያስገኝ ዶክተር ድሪባ አብራርተዋል።
የጋምቤላ ግብርና ምርምር ተቋም ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡቦንግ ኡቦንግ በክልሉ የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮችን የግብርና ቴክኖሎጂ ችግር ለመፍታት ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተለይም በሰብል ልማት በቆሎና ማሽላ፣ በፍራፍሬ በማንጎና ከእንስሳት ዘርፍ ደግሞ በዶሮ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን የማላመድና የማፍለቅ ሥራዎች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ክልሉ ይፋ ያደረገውን የግብርና ሽግግር ፕሮግራም ስኬታማ ለማድረግ የተጠናከረ ሙያዊና የፋይናንስ ድጋፍ እየተደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ተቋማቱ በፈጠሩት ቅንጅት ''ኮኮክ'' የተባሉ የዶሮ ዝርያዎች ተላምደው ወደ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ መሰራጨታቸውን የገለጹት ደግሞ በክልሉ ግብርና ምርምር ተቋም የሥርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አብዮት ዓለማየሁ ናቸው።
ዝርያዎቹ በእንቁላል በዓመት ከ250 በላይ፣ በሥጋ ደግሞ ከአራት ኪሎ ግራም በላይ በመስጠት ከአካባቢው ዝርያዎች በእጥፍ የሚበልጥ ምርት እንደሚሰጡም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል በመኸር ወቅት ከሚከናወኑ የግብርና ሥራዎች በተጨማሪ፣ የበጋ መስኖ ልማትና የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሮች እየተካሄዱ መሆናቸው ይታወቃል።