ቀጥታ፡

ከሊባኖስ 262 ዜጎች በሶስት ዙር ወደ ሃገር ቤት ተመልሰዋል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 15/2016 (ኢዜአ) ፡- የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሊባኖስ ይኖሩ የነበሩ 262 ዜጎች በሶስት ዙር ወደ ሃገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉን በቤይሩት የኢፌዲሪ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በዛሬው እለት በፅህፈት ቤቱ ድጋፍ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከተመቻቸላቸው ዜጎች በሶስተኛው የበረራ ፕሮግራም 88 ዜጎች አዲስ አበባ መግባታቸውን ጽህፈት ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሊባኖስ ረዥም ዓመታት ሲኖሩ የነበሩ ሰነድ አልባ ዜጎች በጥያቄያቸው መሠረት ከሊባኖስ መንግስት ያለ እሥር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄው ለሊባኖስ ኢሚግሬሽን ቀርቦ ለ315 ዜጎች መፈቀዱን ገልጿል፡፡

ዝግጁ ለሆኑት መውጫ ቪዛ ተመቻችቶ በመጀመሪያ የበረራ ፕሮግራም 78 ዜጎች፣ በሁለተኛው የበረራ ኘሮግራም 96 ዜጎች የተመለሱ ሲሆን በሶስተኛ በረራ ፕሮግራም ዛሬ 88 ዜጎች በአጠቃላይ በሶስቱ በረራዎች 262 ዜጎች ወደ አገር ቤት መመለስ ተችሏል ብሏል።

ተፈቅዶላቸው የቀሩት ዜጎች ዕድሉ ሳይቃጠል በአጭር ቀናት ጊዜ ከመጡ ድጋፉ የሚሠጣቸው መሆኑንም አስታወቋል፡፡

በአሠሪዎቻቸው ክስ ምክንያት በዓመቱ ወደ ሀገራቸው መመለስ ላልቻሉ ዜጎች ነፃ የጥብቅና አገልግሎት እንደተመቻቸላቸውም በመረጃው ተጠቁሟል።

ጽህፈት ቤቱ የዜጎችን መብት በማስከበር ሂደት ለተባበሩ ለሊባኖስ መንግሥት የኢሚግሬሽንና ደህንነት መስሪያ ቤት፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት ምስጋና አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም