ኢንስቲትዩቱ በምርምር ያገኛቸውን ዝርያዎች በራሱና በአርሶ አደሩ ማሳ በማባዛት ተደራሽ እያደረገ ነው

ሮቤ፤ ህዳር 15/2016 (ኢዜአ) ፦ የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምርምር ውጤቶችን ከማፍለቅ ባለፈ፤ በምርምር የተገኙ ዝርያዎችን በራሱና በአርሶ አደሩ ማሳ በማባዛት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። 

ኢንስቲትዩቱ በሥሩ ባደራጃቸው የምርምር ማዕከላት የሚያደርጋቸው ምርምሮች በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ከማሳካት በተጓዳኝ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘትን ታሳቢ ያደረጉ መሆኑም ተመላክቷል። 

የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ቦጋለ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የምርምር ውጤቶችን ከማፍለቅ ባለፈ በምርምር የተገኙ ዝርያዎችን በራሱና በአርሶ አደሩ ማሳ በማባዛት ተደራሽ እያደረገ ነው። 

ኢንስቲትዩቱ በሥሩ በሚገኙ 17 ማዕከላት አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በምርምር በማውጣትና በማላመድ አርሶ አደሩ እንዲጠቀምባቸው በማገዝ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እየሰራ ነው ብለዋል። 

አቶ ተሾመ እንዳሉት፣ማዕከላቱ ባለፈው ዓመት ብቻ በሰብል ልማት፣በጥራጥሬና በእንስሳት መኖ ላይ ትኩረት ያደረጉ 19 ቴክኖሎጂዎችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚዎች ማድረሱን ገልጸዋል። 

በምርምር የወጡ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በስፋት ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱ በኢንስቲትዩቱ ማዕከላት፣ በኢንተርፕራይዞችና በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በስፋት እንዲባዙ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት። 

የሲናና ምርምር ማዕከል በሁለቱ የባሌ ዞኖች ውስጥ ለሚገኙ ሞዴል አርሶ አደሮች ከ80 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ያከናወነው የዘር ብዜትም የዚሁ ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል። 

እየተባዙ የሚገኙ የምርምር ዝርያዎች በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ከማገዛቸውም በላይ፣የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንደሚያስችሉ አቶ ተሾመ አስረድተዋል። 

ከማዕከላቱ ያገኙትን የምርምር ውጤቶችን ተቀብለው ከሚያባዙ ተቋማት መካከል የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ አንዱ ነው። 

የቅርንጫፉ ተተኪ ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አስቻለው እንዳሉት፤ ኢንተርፕራይዙ ከሲናና ግብርና ምርምር ማዕከልና ከሌሎች የግብርና ማዕከላት የሚያገኛቸውን ዝርያዎች ከ17 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ እያባዛ መሆኑን አስታውቀዋል። 

የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ኃላፊ አቶ ታመነ ሚደቅሳ በበኩላቸው ማዕከሉ ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ ከ97 የሚበልጡ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚዎች ማድረሱን ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅትም ባለፈው ዓመት በምርምር ያገኘውን " ቦኩ" የሚል ስያሜ የተሰጠውና በሄክታር 72 ኩንታል ምርት የሚሰጥ የስንዴ ምርጥ ዘር በራሱና 80 ሄክታር በሚበልጥ የአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እያባዛ መሆኑን ተናግረዋል። 

የአጋርፋ ወረዳው አርሶ አደር አቶ በየነ ታደሰ በሰጡት አስተያየት ከአምስት ዓመታት በፊት ምርጥ ዘርና የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን እምብዛም ተግባራዊ ሳያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። 

በዚህም በስንዴ ከሄክታር ከ15 ኩንታል የዘለለ ምርት አግኝተው እንደማያውቁ ገልጸዋል። 

ባለፈው ዓመት የመኽር ወቅት ማዕከሉ ያገኙትን "ሳነቴ" የሚባል የስንዴ ዝርያ በማምረት ግን በሄክታር 60 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል። 

በመኸር ወቅት በመሥመር የመዝራት ቴክኖሎጂን ጨምሮ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም ከማዕከሉ ያገኙትን 'ቦኩ" የሚባል የስንዴ ዝርያ በአንድ ሄክታር ላይ አልምተው እየተንከባከቡ መሆኑን ገልፀዋል። 

አርሶ አደር በቀለ አሰፋ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ሰብልን በወቅቱ በማረምና የአረም መከላከያ መድኃኒትን በመርጨት ረገድ ክፍተት ስለነበረ የልፋታቸውን ያህል ምርት ሳያገኙ  መቆየታቸውን አስታውሰዋል። 

በአሁኑ ወቅት የማዕከሉ ተመራማሪዎች በሚሰጧቸው ምክር በመታገዝ ማሳቸውን በማረምና በወቅቱ የአረም መከላከያ መድኃኒት በመርጨት በሄክታር እስከ 70 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በአሁኑ ወቅት ከ1ሺህ 400 በሚበልጡ መስኮች ላይ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም