የክልሉ መንግስት ድህነት ቀናሽ ለሆኑ ዘርፎች ከ63 በመቶ በላይ በጀት መድቦ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ መንግስት ድህነት ቀናሽ ለሆኑ ዘርፎች ከ63 በመቶ በላይ በጀት መድቦ እየሰራ ነው
ሐዋሳ ህዳር 15/2016 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል ድህነት ቀናሽ ለሆኑ ሴክተሮች ከፍተኛ በጀት ተመድቦ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች እየከተናወኑ መሆኑን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ፡፡
በመሰረታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥና በማህበራዊ ተጠያቂነት ትግበራና ድጋፍ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በሃዋሳ ተካሂዷል፡፡
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አራርሶ ገረመው በዚህ ጊዜ እንደገለጹት በመንግስት የሚመደበውን ውስን ሃብት ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው አሰራር በመጠቀም የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት መስራት ይገባል፡፡
የክልሉ መንግስት ድህነት ቀናሽ ለሆኑ ሴክተሮች ከፍተኛ በጀት መድቦ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ድህነት ቀናሽ ለሚባሉት እንደ መንገድ፣ ውሃ፣ ግብርና፣ትምህርትና ጤና ሴክተሮች በየዓመቱ ከአጠቃላይ በጀቱ 63 ከመቶ በላይ በጀት እንደሚመደብም ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመትም የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝን ጨምሮ 63 ነጥብ 4 ከመቶ በጀት ተመድቦ የህዝቡን ጥያቄ መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ክልሉ እንደ አዲስ በተደራጀባቸው ባለፉት ሶስት ዓመታትም የህዝብን የረዥም ጊዜ የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ መፍታት የሚያስችል ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 38 ከመቶ ከነበረበት ወደ 56 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለ ገልጸው በትምህርት ዘርፍ የተጀመረው ስራም ባለሃብቱን እና ህዝቡን ያሳተፈ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም በቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ የተጀመረው የንቅናቄ ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከአለም ባንክ ባገኘው ድጋፍ የሚተገበረው ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም በክልሉ በሚገኙ 12 ወረዳዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ሃይሌ አርሲሳ ናቸው፡፡
ፕሮግራሙ ድህነት ቀናሸ በሆኑ ሴክተሮች ላይ ትኩረት አድርጎ የአገልግሎት አሰጣጡንና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ተግባር የሚከናወንበት ነው ብለዋል፡፡
ፕሮግራሙ ተግባራዊ በተደረገባቸው ወረዳዎች የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በአለም ባንክ ድጋፍ ከሚደገፉ 8 ወረዳዎች በተጨማሪ የክልሉ መንግስት በራሱ በጀት ፕሮግራሙን በአራት ወረዳዎች ማስጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ማኔጅመንት ኤጄንሲ የአቅም ግንባታ ባለሙያ ወ/ሪት ቤተልሄም ጌታቸው ፕሮግራሙ በመላው ሃገሪቱ በሚገኙ 412 ወረዳዎች እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በወረዳዎቹ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና አደረጃጀቶች የተውጣጡ ህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመወያየት መፍትሄ የሚመላከትበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም የሲዳማ ክልል አስተባባሪ አቶ ዘለቀ ዶራ በበኩላቸው ፕሮግራሙ ተግባራዊ በሆኑባቸው ወረዳዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች የተካተቱበት ኮሚቴ መዋቀሩን ተናግረዋል፡፡፡
በይርለም፣ በሸበዲኖና በአለታ ወንዶ ወረዳዎች የትምህርት ቤትም ሆነ የተለያዩ ህንጻ ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ኮሚቴዎቹ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በመልጋ ወረዳ የማህበራዊ ተጠያቂነት ኮሚቴ አባል የሆኑት አርሶአደር ተሾመ ሌላሞ ህብረተሰቡን ወክለው በተለያዩ የልማት ስራዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር ከመንግት አካላት ጋር እንደሚወያዩ ተናግረው በዚህም የውሃ፣ የትምህርት፣ የመንገድና ሌሎች ችግሮቻቸው መፍትሄ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ድህነት ቀናሽ በተባሉ ሴክተሮች የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በመልጋ ወረዳ በሚገኙ የጤናና የትምህርት ተቋማት የመስክ ምልከታ ተደርጓል፡፡