ፓኪስታን የብሪክስ/BRICS/ አባል ለመሆን ጥያቄ አቀረበች

217

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 14/2016 (ኢዜአ) ፦ ፓኪስታን የብሪክስ አባል ሀገራትን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረቧን የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ብሪክስ ለታዳጊ አገራት ጠቃሚ ቡድን መሆኑንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመልክቷል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ሙምታዝ ዛህራ ባሎክ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ፓኪስታን የብሪክስ አባል ለመሆን ጥያቄ ማቅረቧን አረጋግጠዋል።


 

ሀገሪቱ የቡድኑ አባል ለመሆን ጥያቄ ያቀረበችው ቡድኑ ግልጽነት የተሞላበት፣ ብዙሃኑን ያቀፈና አካታች በመሆኑ መሆኑንም ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል።

በዚህም ፓኪስታን የቡድኑ አባል ብትሆን በቀጣይ ለሚፈጠረው አለም አቀፍ ትብብር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራት አብራርተዋል።

ፓኪስታን ከብዙዎቹ የብሪክስ አባል ሀገራት እንዲሁም ከአዳዲሶቹ ጥያቄ ያቀረቡ አገራት ጋር ወዳጅነት እንዳላት መግለጻቸውን ዥንዋ አስነብቧል።

ቃል አቀባይዋ አክለውም “ቡድኑ ፓኪስታን ያቀረበችው የአባልነት ጥያቄ የትብብርና አብሮ የመለወጥ ፍላጎት የያዘ ጥያቄ መሆኑን መሰረት አድርጎ ቀና ምላሽ እንደሚሰጠን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።

ብሪክስ በአሁኑ ወቅት በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የተካተቱበት የኢኮኖሚ ቡድን ሲሆን በነሀሴ ወር በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 15ኛው የቡድኑ የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን፣ የኢራንን፣ የአርጀንቲናን፣ የግብፅን፣ የሳዑዲ አረቢያንና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን የአባልነት ጥያቄ መቀበሉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም