የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እና የህንድ ብሔራዊ ፎረንሲክ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በትብብር ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እና የህንድ ብሔራዊ ፎረንሲክ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በትብብር ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 14/2016 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እና የህንድ ብሔራዊ ፎረንሲክ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በትብብር መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱም በትምህርትና ስልጠና፣ በመምህራን አቅም ግንባታ እና በማማከር ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ያለመ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የህንድ ብሔራዊ የፎረንሲክ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በዓለም ላይ ምርጥ ከሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱና በፎረንሲክ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ዩኒቨርሲቲ መሆኑም ተጠቁሟል።
በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው በዘመናዊ ተክኖሎጂና በዕውቅ ተመራማሪዎች የተደራጀና በፎረንሲክ ሳንይንስ በርካታ የልህቀት ማዕከሎችን የገነባ ተቋም መባሉን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በርካታ የልህቀት ማዕከሎችን በማቋቋም፣ በህንድ ከስምንት በላይ ካምፓሶችን በመክፈት የማስተማር፣ የማሰልጠን፣ የምርምርና የማማከር ስራዎችን እያከናወነ ያለ መሆኑም ተገልጿል።
በተጨማሪም ከሀገር ውጭ በኡጋንዳ ተጨማሪ ካምፓስ በመክፈት ተመሳሳይ ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝም በመረጃው ተመላክቷል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በካምፓቹ ውስጥ ከ33 በላይ ትምህርት ቤቶችንና ዲፓርትመንቶችን እንዲሁም ከ102 በላይ ፕሮግራሞችን በመክፈት በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ የፎረንሲክ ሳይንቲስቶችን እያፈራ ያለ መሆኑም ተጠቁሟል።
ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ80 በላይ ሀገራት ተማሪዎችን በተለያዩ ፕሮግራሞች በስኮላርሽፕ ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እያስገነባ ያለውን የፎረንሲክ ሳይንስ ኮሌጅን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ በሚያደረገው ጥረት የህንድ ብሔራዊ የፎረንሲክ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ቴክኒካዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።
በዚህም በማማከር፣ በመምህራንና የባለሙያ አቅም ግንባታ ላይ ድጋፍ ለማድረግ ፍቃደኛ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ምክትል ቻንሰለር ዶክተር ጄ.ኤም. ቪያስ በስምምነቱ ወቅት ማረጋገጣቸውን በመረጃው ተጠቁሟል፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ እና የህንድ ብሔራዊ ፎረንሲክ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቻንስለር ዶክተር ጄ.ኤም. ቪያስ መፈረማቸውም ተገልጿል።