በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርታማነትን መጨመር የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው 

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 14/2016 (ኢዜአ) ፦  በሰው ሰራሽ አስተውሎት ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎት በመስጠት ምርታማነትን መጨመር የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

ውጤታማነታቸው በሙከራ የተረጋገጠ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የምርምር ውጤቶች በቅርቡ ይፋ ሆነው ሥራ ላይ ይውላሉም ብሏል፡፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዳታን መሰረት በማድረግ የሰው ልጆችን ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ቋንቋና እሳቤ በላቀ አረዳድና ግንዛቤ ተክቶ ለችግሮች መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሁለንተናዊ አገልግሎት በዓለም ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገና እየዘመነ መጥቷል። 

በኢትዮጵያም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በ2012 ዓ.ም ተቋቁሞ መስከረም 10 ቀን 2013 ዓ.ም ተመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና ለኢዜአ እንዳሉት፤ ለግብርና፣ ለትምህርት፣ ለጤና እንዲሁም ለኅብረተሰብ ጥበቃና ደኅንነት የሚውሉ የምርምር ውጤቶች እየመጡ ነው፡፡

በኢንስቲትዩቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዳታ ማዕከል ተገንብቶ ለመንግስትና ለግሉ ዘርፍ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጤናውን ዘርፍ ባለሙያዎች የሚያግዙ የምርምር ውጤቶችን ማፍለቅ እንዲሁም ማሽንን አገርኛ ቋንቋዎች በማስተማር የተለያዩ ስራዎችን ማከናወን ተችሏልም ብለዋል፡፡

በትራንስፖርት ዘርፉ "የኤሌክትሮኒክ ካርጎ ትራኪንግ ሲስተም" የተባለ የምርምር ሥራ በቅርቡ አገልግሎት ላይ እንደሚውልም ገልጸዋል፡፡

የወንጀል መከላከል ዘርፍን የሚያግዙ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የምርምር ውጤቶች በቅርቡ ይፋ እንደሚደረጉም ገልጸዋል፡፡


 

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ግርማ በበኩላቸው በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ አምስት አገርኛ ቋንቋዎች ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥራ ላይ መዋላቸውን ጠቅሰው፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሁሉንም ቋንቋዎች ተደራሽ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም