በኢትዮጵያ በሩብ ዓመቱ የቱሪስት ፍሰቱ ጨምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በሩብ ዓመቱ የቱሪስት ፍሰቱ ጨምሯል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 14/2016 (ኢዜአ) ፦ በ2016 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የቱሪስት ፍሰቱ የተነቃቃና በቁጥርም የጨመረ እንደነበር የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።
የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የመንግሥት የሥራ አፈጻጻምን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተገምግሟል፡፡
በዚህም በተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች የተሻለ አፈጻጻም መመዝገቡ ነው የተገለጸው፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንደገለጹትም በሩብ ዓመቱ የአለም አቀፍና የሀገር አቀፍ የቱሪስት ፍሰት ቁጥር ጨምሯል፡፡
ለዚህም ተጠናቀው ወደ ስራ የገቡና በመግባት ላይ ያሉ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በሌላ መልኩ ከፍተኛ ቱሪስት ፍሰትን ካስተናገዱ አካባቢዎች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአገር ውስጥ የቱሪዝም ፍሰትም ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ በሩብ ዓመቱ ከ8 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የቱሪዝም መስህቦችን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።
ሚኒስቴሩ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎች የማስተዋወቅ ሰፊ ስራ መስራቱን አብራርተዋል።
መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተከፈተው ሀገር አቀፍ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ ለዘርፉ መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ የፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ እንዳሉትም በሩብ ዓመቱ የተለያዩ በዓላት ትውፊታቸውን ይዘው እንዲከበሩ ከማድረግ አንጻር የተጠናከረ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ አሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል ፣ መስቀል፣ ኢሬቻ ፣ ያሆዴ፣ ጊፋታ፣ የየም እና የከፊቾ የዘመን መለወጫን ጨምሮ ሌሎችም በዓላት ባህላዊ ትውፊቶችን በጠበቀ መልኩ እንዲከበሩ ከክልሎች ጋር መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
በዓላቱም የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ከማድረግ ባሻገር ኢኮኖሚው እንዲነቃቃም ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው በሩብ ዓመቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡
ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ30 በመቶ በላይ ብልጫ ያለው መሆኑንም አክለዋል፡፡
120ሺህ የሚሆኑ ዜጎችን ወደ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጪ አገራት መላክ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡