ቀጥታ፡

የመቱ መሬት አስተዳደር ፅህፈት ቤት የፋይል አያያዝና የአገልግሎት አሰጣጥ አለመዘመን ለእንግልት ዳርጎናል - ባለጉዳዮች

መቱ፤ሕዳር 14/2016 (ኢዜአ)፡ - የመቱ ከተማ መሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የፋይል አያያዝና አገልግሎት አሰጣጥ ባለመዘመኑ ምክንያት ለምልልስና እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን ባለጉዳዮች ገለፁ።

የመቱ ከተማ መሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ተገልጋዮች የሚያነሱት ቅሬታ ትክክል መሆኑን ተቀብሎ በተለይም የመሬት ባለይዞታዎች የግል ማህደር የማዘመንና እየተገባደደ ያለው የካዳስተር ምዝገባ ለቅሬታው መፍትሔ እንደሚሰጥ ገልጿል። 

የማህደር ፍለጋ መራዘምና አንዳንዴም መጥፋት ለተጋጋሚ ቀጠሮና ላልተገባ ወጪ እየዳረጋቸው መሆኑን የሚያነሱት ባለጉዳዮች ለቀናት ስራ ፈተው እንዲመላለሱ እያስገደዳቸው መሆኑን አንስተዋል። 

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ታፈሰ ተፈሪ እንዳሉት የሚጠበቅባቸውን ዓመታዊ ክፍያ በጊዜው ለመፈፀም ወደ ጽሕፈት ቤቱ ያመሩት ከሳምንት በፊት መሆኑን ይናገራሉ።

ነገር ግን ማኅደራቸው በዚህ ጊዜ ውስጥ ባለመገኘቱ ለተከታታይ አምስት ቀናት እየተመላለሱ መሆናቸውን አክለዋል።

በጽሕፈት ቤቱ በየዕለቱ የተለያዩ አገልግሎቶችን ፈልገው የሚሄዱ ሰዎች ቁጥርና አገልግሎቱን የሚሰጡ ሰዎች ያለመመጣጠንም ችግሩን አባብሶታል ባይ ናቸው አቶ ታፈሰ።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ቤካ ታረቀኝ በበኩላቸው የይዞታ ማኅደራቸው ወጥቶ የእግድ ደብዳቤ እንዲፃፍላቸው ፈልገው ወደ መስሪያ ቤቱ ከሄዱ ሳምንት አልፏቸዋል።

በፋይል መጥፋትና ጽህፈት ቤቱ በሚሰጠው ቀርፋፋ አገልግሎት ምክንያት ምልልሱ እያታከታቸው መሆኑን አክለዋል።

በዚህ ላይ ማኅደሩን የሚያወጡ የመዝገብ ቤት ሰራተኞች እጅግ ውስን መሆናቸው በዕለቱ ለአገልግሎት የሚመጣውን ተገልጋይ ለማስተናገድ ሲቸገሩ ማየታቸውንም አንስተዋል።

የከተማው መሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተገልጋይ የሚስተናገድበት መስሪያ ቤት ቢሆንም በተጨባጭ የሚስተዋለው ግን የሰራተኛ እጥረት ችግር መኖሩን ነው ያሉት ደግሞ አቶ አብዮት ረጋሳ ናቸው።

ለበርካታ ተገልጋይ የክፍያ ተመን የሚወጣውም ሆነ ደረሰኝ የሚሰጠው በአንድ ሰራተኛ ብቻ በመሆኑ የተቀላጠፈና ብዙዎችን ተደራሽ የሚያደርግ አገልግሎት እንዳይሰጡ እንቅፋት መሆኑን መታዘባቸውንም አንስተዋል።

በአጠቃላይ የከተማው የመሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የተገልጋይ ማኅደር አያያዙን ያላዘመነ መሆኑና አገልግሎት የሚሰጡ ሰራተኞች ከተገልጋዩ ጋር የማይመጣጠን መሆን ተገቢውን አገልግሎት እንዳያገኙና ለእንግልት እንዲዳረጉ እያደረጋቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

መስሪያ ቤቱ የማኅደር አያያዙን በማዘመን የተቀላጠፈ የደንበኞች አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን እርምጃ በመውሰድ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት እንዳለበትም በማመልከት።

የመቱ ከተማ መሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ስመኝ ሙሉጌታ በበኩላቸው ተገልጋዮቹ ያነሱት ቅሬታ ትክክል መሆኑን አንስተዋል።

ችግሩ መስሪያ ቤቱ ካለው የሰው ኃይል እጥረት ጋር የሚያያዝ መሆኑን አንስተው፤ በተለይም ወቅቱ ተገልጋዮች ክፍያ የሚፈፅሙበት ወር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሩ የሰፋ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህንንም ችግር ለመፍታት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት ስራ መጀመሩን ገልጸው ምፍተሄው ይበጅለታል ብለዋል።

የከተማውን የመሬት ባለይዞታዎች ማኅደር በማዘመን የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እየተከናወኑ ያሉ በርካታ ስራዎች መኖራቸውን አንስተው ዘመናዊ መሬት አስተዳደር ወይም ካዳስተር ስራው በመገባደድ ላይ መሆኑንና ይህም የሚነሳውን ቅሬታ እንደሚፈታ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም