ቀጥታ፡

ሬዶ የባህልና የአገር በቀል እውቀቶች ማዕከል የአፋርና የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ የተንጸባረቀበት ነው

ሰመራ፣ ህዳር 14/2016 (ኢዜአ)፦በሰመራ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ሥራ የጀመረው ሬዶ የባህልና የአገር በቀል እውቀቶች ማዕከል የአፋር ብሎም  የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ የተንጸባረቀበት ነው ሲሉ ማዕከሉን የጎበኙ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የተከፈተው ማዕከል የአፋር ህዝብ ታሪክ፣ ህዝቡ ከጥንት ጀምሮ ሲገለገልባቸው የነበሩ መሳሪያዎች፣ የተለያዩ ቅርሶች፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ አገር በቀል ዕውቀቶቹና ትውፊቶቹ ባንድ ላይ የተሰባሰቡበት ነው።

በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ የሰመራ፣ ወሎ፣ ወልዲያ እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ሰሞኑን በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ የተሳተፉ ምሁራን ማዕከሉን ጎብኝተዋል።

ማዕከሉን ከጎበኙት መካከል የራያ ዮኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር መብራህቱ ንጉስ በማዕከሉ የአፋር ህዝብ ታሪክና ቅርስ በአግባቡ ተደራጅቶ ማየታቸውን ተናግረዋል።

"የአፋር ክልል የሰው ዘር መገኛ እና የኢትዮጵያ መገለጫ ነው" ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር መብራህቱ፣  የክልሉ ህዝብ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ በማዕከሉ በአግባቡ መሰናዳቱ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

በእዚህ በኩል ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጠንካራ ሥራ እየሰራ እንደሆነ በጉብኝቱ ወቅት እንደተመለከቱና ይህም መበረታታት እንዳለበት ገልጸዋል።


 

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አለማየሁ እርቅይሁን በበኩላቸው፣ "ማንም ኢትዮጵያዊ ማዕከሉን ሲጎበኝ 'የአፋር ታሪክ የኔም ታሪክ ነው' ብሎ እንዲያስብ የሚያደርግ ነው" ብለዋል።

በማዕከሉ የተመለከቱት የአፋር ህዝብ በአገረ መንግስት ግንባታ ላይ ሚናው የጎላ መሆኑን ለመረዳት ያስችላል ሲሉም ገልጸዋል።    

በማዕከሉ የተሰባሰቡ ሀብቶች ከክልሉ ባለፈ የመላው ኢትዮጵያዊያ የጋራ እሴቶችና ታሪክ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ምሁራን በራሳቸው ምርምር እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ኘሬዚዳንት ዶክተር ሱልጣን መሐመድ በበኩላቸው በማዕከሉ እንደ ሐገር ጠቃሚ የሆኑ እሴቶችን በማየታቸው መደሠታቸውን ገልፀዋል።

የአፋር ክልል የሰው ዘር መገኛ እና የበርካታ ቅርሶች ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው፣ በማዕከሉ የህዝቡን  ባህላዊ ቁሶች፣ ታሪኩን፣ ጥንታዊ አሰፋፈሩንና ማህበራዊ ትስስሩን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር አበራ ሰማው በበኩላቸው በማዕከሉ ነባር የአፋር ህዝብ ዕውቀቶችን በአግባቡ ከመሰነድ ባለፈ እሴቶቹና ህግጋቶች የተንጸባረቁበት መሆኑን ማየታቸውን ጠቅሰዋል። 


 

የህዝቡን ቁሳዊ የሆነውን ብቻ ሳይሆን ትውፊቶች፣ ቅርሶች እንዲሁም እንዲሁም ህግጋቶቹ ጭምር የተሰባሰቡበት መሆኑ ለሌላው ያስተምራል ሲሉ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም