ቀጥታ፡

ሙስናን ለመከላከል የሲቪክ ማህበራት፤ የኃይማኖትና የትምህርት ተቋማት በአመለካከት ግንባታ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባቸው - አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 14/2016 (ኢዜአ) ፦ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የሲቪክ ማህበራት፤ የኃይማኖትና የትምህርት ተቋማት በአመለካከት ግንባታ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በዓለም ለ21ኛ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን አክብረዋል፡፡


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በመደረኩ እንደገለጹት፤ ሙስና የልማት፤ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፤ የህግ የበላይነት መከበርና የህዝቦች ዘላቂ ሰላምና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጠንቅ ነው፡፡

ሙስና የዓለም ሀገራትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መሰረት በማናጋት ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት የጸረ ሙስና ኮንቬንሽን ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያም የተመድን የጸረ ሙስና ኮንቬንሽንና እና የአፍሪካ ህብረትን የጸረ ሙስና መዋጊያና መከላከያ ኮንቬንሽን በመፈረም የጸረ ሙስና ትግሉን ቀደም ብላ መጀመሯን አስታውሰዋል፡፡

በተለይም ባለፉት ዓመታት መንግስት የጸረ ሙስና ግብረ ኃይል በማቋቋም ሙስናን የመከላከል ስራ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል ብለዋል፡፡

መንግስት ሙስና በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመገንዘብ ሙስናን መከላከል የሚያስችል አመቺ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

ሙስናና ብልሹ አሰራርን መከላከል ለመንግስት ወይም ለተወሰኑ ቡድኖች ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት አምባሳደር ብርቱካን፤ በየደረጃው ያሉ የመንግስትና የግል ተቋማትን የነቃ ተሳትፎ እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡

በተለይም የሲቪክ ማህበራት፣ የኃይማኖትና የትምህርት ተቋማት በአመለካከት ግንባታ ላይ በመስራት የጸረ ሙስና ትግሉን ማገዝ አለባቸው ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የተቋሙ ሰራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ሰዓታቸውን በማክበር፣ የተረከቡትን ሀብት በአግባቡ በመያዝና በመጠቀም እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በማቀላጠፍ ከሙስና የጸዳ ስራ ማከናወን ይገባል ነው ያሉት፡፡


 

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው በበኩላቸው ሙስና በተለያዩ አገራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ከመፍጠር አልፎ የሉዓላዊነት ስጋት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓለም ላይ በተለያየ ደረጃ የሚገለጹ የሙስና አይነቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኛው ሀገራት ፈተና የሆነው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚፈጸም ሙስና ነው ብለዋል፡፡

በፌዴራልና በክልሎች የጸረ ሙስና ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ስራ ከጀመረ በኋላ በጸረ ሙስና ትግሉ ተስፋ ሰጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም 2015 በጀት ዓመት በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ስራ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እንዲሁም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬት እንዲመለስ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ 812 ሚሊዮን ብር እና 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬት ተመላሽ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያን በ2023 የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ "ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው በህብረት እንታገል" የሚለውን መሪ ቃል በተግባር ማከናወን ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም