ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ አንድነትና የህዝቦችን አብሮነት ማጠናከር ላይ ማተኮር አለባቸው

ቦንጋ፣ ጂንካ ፤ ህዳር 14/2016 (ኢዜአ) ፦  መገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ አንድነትና የህዝቦችን አብሮነት ማጠናከር ላይ አተኩረው በመስራት የጋራ ትርክት መገንባት እንዳለባቸው የዘርፉ ምሁራንና ባለሙያዎች ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ መገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ ''ሚዲያ አጥፊም፣ አልሚም ነው፣ ዋናው ሊጠየቅ የሚገባው ወሳኝ ጥያቄ ግን ማን ለምን ዓላማ አዋለው የሚለው ነው'' ብለው ነበር። 

ይህንኑ መነሻ በማድረግ መገናኛ ብዙሃን የህዝቦችን አብሮነትና ትስስር ከማጎልበት አኳያ ምን አይነት ሚናን እየተጫወቱ ይገኛሉ? በሚል የዘርፉ ባለሙያዎችን ጠይቀናል።    

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ትምህርት ምሁራንና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መገናኛ ብዙሃን ሃገራዊ አንድነትና የህዝቦችን አብሮነት ማጠናከር ላይ አተኩረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር በረከት ወንድሙ እንዳሉት መገናኛ ብዙሃን ዓለም አቀፍ ተፅእኖ መፍጠር የሚችል አቅም አላቸው።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃንም ይህንን አቅማቸውን ተጠቅመው አንድነትና አብሮነት ላይ አተኩረው በመስራት የጋራ እና አሰባሳቢ ትርክት መገንባት አለባቸው ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን ሰላም እንዲሰፍን፣ አገራዊ አንድነት እንዲጠናከርና የህዝቡ ትስስር እንዳይላላ የሚያደርጉ ስራዎች ማጉላት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

መገናኛ ብዙሃን ከአካባቢያዊ አስተሳሰብ በመውጣት ሀገራዊ ትርክትንና አንድነትን ከማጠናከር አኳያ አሁንም ብዙ ጉድለቶች እንደሚታዩ ገልጸው ይህ አካሄድ መስተካከል እንዳለበትም መክረዋል።


 

የመገናኛ ብዙሃን ህዝቡን ወደ አንድ የማሰባሰብ አቅም እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ የጅንካ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና የስነ-ተግባቦት መምህር ሀይሬዲን ሙሐመድ ናቸው።

ብሔራዊ ጥቅምን የመጠበቅ፣ በማህበረሰቡ ዘንድ አዎንታዊ አስተሳሰቦችና ተግባቦቶችን የሚፈጥሩ መረጃዎች የመገንባት ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ከብሔራዊ ጥቅምና አሰባሳቢ ትርክት ላይ ያላቸው ትኩረት ያነሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም የመገናኛ ብዙኃን የሀገርን ምስጢር፣ ብሔራዊ ጥቅም የመጠበቅና ማህበረሰቡን በመልካም ስዕብና የመገንባት መርሆችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊሰሩ እንደሚገባ መምህር ሀይሬዲን ተናግረዋል። 

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኛ ወንድሙ ካኪሎ በበኩሉ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት ለችግሮቹ የመፍትሔ አካል መሆን አለባቸው ብለዋል።


 

‘‘የህዝቡን ስነ-ልቦዊ አንድነት የሚሸረሽሩ የጥላቻ ትርክቶች ለማስተካከል የመገናኛ ብዙሃን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መስራት አለብን’’ ሲል ተናግሯል።

በተለይም አንድነትን የሚያጎለብቱ አስታራቂና የጋራ የሆኑ ትርክቶች በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲጎለብቱ ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግሯል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም