ቀጥታ፡

ፍትሕ ሚኒስቴር እና አይ ኦ ኤም የስደተኞች አስተዳደር ሥርዓትን ለማሳለጥ የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 13/2016 (ኢዜአ)፦ የፍትሕ ሚኒስቴርና ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) የስደተኞች አስተዳደር ሥርዓትን ማሳለጥ የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው እና በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) የኢትዮጵያ ተልዕኮ ሊቀመንበር አቢታቱዋ ዋኔ ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡

በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ተልዕኮ ሊቀመንበር አቢታቱዋ ዋኔ፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ዓለም አቀፍ መርህን በተከተለ መንገድ መቀበል የሚያስችል ሪፎርም በማድረግ  በተለያዩ የሀገሪቱ በሮች በየዓመቱ በርካታ ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት እና በፍትሕ ሚኒስቴር መካከል የተፈረመው የትብብር ስምምነትም ውጤታማ የስደት አስተዳደር ሥርዓትን በማስፈን በቀጣናው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ ለመያዝ ያግዛል ብለዋል፡፡

በቀጣናው ግጭት፣ ድህነትና የተፈጥሮ አደጋ ለዜጎች ሕገ-ወጥ ስደትና እንግልት ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በሚሊየን የሚጠጉ ስደተኞችን የምታስተናግድበት መንገድ ለሌሎች መማሪያ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በማውጣት፣ ትብብርና ተጠያቂነትን በማስፈን የስደተኞችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የምታደርገው  ጥረት የሚበረታታ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅትም ኢትዮጵያ ለምታከናውነው ተግባር የሚያደርገውን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የስደት ፖሊሲ በማርቀቅና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በማውጣት በትኩረት እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትን መሠረት ያደረገ አካሄድ በመከተል ተቋማዊና ብሔራዊ አቅሟን በተለያዩ አግባቦች እየገነባች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የትብብር ስምምነቱም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የስደተኞች ደኅንነትና ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ አሠራር ውጤታማ ለማድረግ ያግዛልም ነው ያሉት።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን፤ መንግሥት በመልሶ ማቋቋምና የሥራ ዕድል ፈጠራ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ አይ ኦ ኤም በዚህ ረገድ እገዛና ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም