ዩኒቨርሲቲው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዘመናዊና ቀልጣፋ አሠራር ለመዘርጋት የተጀመሩ ጥረቶችን ያግዛል- ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 13/2016 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በተለያዩ ዘርፎች ዘመናዊና ቀልጣፋ አሠራር ለመዘርጋት የተጀመሩ ጥረቶችን የሚያግዝ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ገለጹ፡፡ 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡ 


 

በጉብኝቱ በሰው ሠራሽ አስተውሎት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን፣ የጤና አገልግሎትን ለማሳለጥና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አድንቀዋል። 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በዚሁ ወቅት፤ ኢንስቲትዩቱ ሀገር ከዘርፉ የምትፈልገውን አበርክቶ ለማሳካት በትክክለኛው መንገድ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የኢንስቲትዩቱን ሥራዎች በተለያየ መልኩ ከማገዝና መደገፍ ባለፈ በሰው ኃብት ልማት የድርሻችንን ለመወጣት እንሰራለን ብለዋል።

በዘርፉ የግብርና፣ ቱሪዝም፣ ጤና  እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ዘመናዊና ቀልጣፋ አሠራር ለመዘርጋት የተጀመረው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዘመናዊና ቀልጣፋ አሠራር ለመዘርጋት የተጀመሩ ጥረቶችን ያግዛል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በተለያዩ ዘርፎች ዘመናዊና ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን የተጀመሩ ጥረቶችን ዩኒቨርሲቲው እገዛና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተቋማዊ ለውጥ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ወንድወሰን ሙሉጌታ፤ በተቋሙ እየተከናወኑ ያሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተግባራትን አድንቀዋል።


 

በጉብኝታቸው የተመለከቱት የዳታ ማዕከልም ከሁሉም ተቋማት ለሚሰበሰቡ መረጃዎች እንደ ቋት የሚያገለግል ትልቅ የሀገር ኃብት መሆኑን አንስተዋል።    

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በርካታ አገራዊ ፕሮጀክቶችን በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡


 

በሁሉም የትምህርት ክፍል ያሉ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ለኢንስቲትዩቱ የበኩላቸውን በማበርከት ላይ በመሆናቸው አመስግነው፤ ይህንኑም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በ2012 ዓ.ም ተቋቁሞ መስከረም 10 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ መርቀው ሥራ ማስጀመራቸው ይታወሳል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም