በኦሮሚያ ክልል ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 1 ነጥብ 8 ቢሊዬን ብር ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 1 ነጥብ 8 ቢሊዬን ብር ገቢ ተሰበሰበ
ህዳር 13/2016(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 1 ነጥብ 8 ቢሊዬን ብር ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ገለጹ።
"ቃላችንን እናድሳለን'' በሚል መሪ ሀሳብ ያለፈው ዓመት የሕዳሴው ግድብ የገቢ ማሰባሰብ ዕቅድ አፈጻጸምና የዚህ ዓመት ዕቅድ ግምገማ ተካሄዷል።
በዚሁ ጊዜ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንትና በክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሰብሳቢ አቶ አወሉ አብዲ የክልሉ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ በተለያየ መንገድ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
ህዝቡ የሕዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይና አንድነትን ያጠናከረ የልማት ፕሮጀክት መሆኑን ተረድቶ ድጋፉን ማጠናከሩንም ጠቅሰዋል።
ለእዚህም በ2015 ዓ.ም ለግድቡ ግንባታ ማስፈጸሚያ የሚውል ከህብረተሰቡ 1 ነጥብ 8 ቢሊዬን ብር ገቢ ማሰባሰብ እንደተቻለ ገልጸዋል።
ዘንድሮም 1 ነጥብ 2 ቢሊዬን ብር ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
የክልሉ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ በገንዘብና በአይነት ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር ግድቡን ከደለል ለመከላከል የችግኝ ተከላ ሥራ በስፋት እያከናወነ መሆኑንም አቶ አወሉ አንስተዋል።
በቀጣይም የግድቡ ግንባታ ፍጻሜውን እስከሚያገኝ ድረስ የክልሉ ህዝብና አመራሩ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋሉ ሲሉ አረጋግጠዋል።
በክልሉ ዘንድሮ ለመሰብሰብ የታቀደውን ገቢ ለማሳካት ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ የልማት ተቋማት፣ ባለሀብቶች እና አትሌቶች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው ለሕዳሴው ግድብ እስከዛሬ ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።
ተሳታፊዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ህዝቡ ከተባበረና በአንድነት ከተነሳ የማያሳካው የልማት ዕቅድ እንደሌለ ያሳየ ትልቅ ጅሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ግድቡ የሀይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ጀምረው መፈጸም እንደሚችሉ ያሳየም መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በቀጣይ በየተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የበኩላቸውን አስተዋጾ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ መንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ኃላፊዎች እንዲሁም ባለሀብቶችና አትሌቶች ተሳትፈዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በተያዘው የህዳር ወር ከዞኑ ነዋሪዎች 44 ሚሊዮን ብር ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፍ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱ ተመላክቷል።
እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም 23 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በቦንድ ግዥ የተሰበሰበ ሲሆን፤ በጥሬ ገንዘብ ደግሞ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል።