ቀጥታ፡

የካፒታል ገበያን ስኬታማ ለማድረግ የኦዲት ሥርዓትን ዘመናዊ፣ ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ ማድረግ ይገባል -ዶክተር እዮብ ተካልኝ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/2016(ኤዜአ)፦ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ስኬታማ ለማድረግ የኦዲት ሥርዓትን ዘመናዊ፣ ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ ማድረግ ይገባል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ገለጹ። 

የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ያዘጋጀው በኢትዮጵያ የኦዲት ትግበራ ባህል የተመለከተ የግምገማ መድረክ የኦዲት ድርጅት አመራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።  

በኦዲት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ዛሬ የተጀመረው ውይይት በነገው እለትም ይቀጥላል።

በዛሬው መድረክ የኦዲት ትግበራ ባህል ላይ በዳሰሳ ጥናት የተለዩ ችግሮች ቀርበው የኦዲት ባለሙያዎችና የኦዲት ድርጅት አመራሮች አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል። 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታና የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር እዮብ ተካልኝ፤ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት የሒሳብና ኦዲት አገልግሎት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል። 

የካፒታል ገበያ ማቋቋምና የውጭ  ባንኮች  እንዲገቡ በመፈቀዱ ከዚህ  አኳያ  ጥራት ያለው የፋይናንስና ኦዲት ሪፖርት ወሳኝ መሆኑንም ነው ያስረዱት። 

የኦዲት ባለሙያዎች ዘመኑ የደረሰበት ጥራት ያለው የኦዲት ተግባራትን ለማከናወን እንዲችሉ ጥራት ያለው የኦዲት ሥርዓት በመዘርጋት ለፋይናንስ ሥርዓቱ ጤናማነት መረጋገጥ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። 

የኦዲት ጉዳይ ሥነ-ምግባር ካልታከለበት ለብልሹ አሠራር የመዳረግ ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ በዚህ ረገድ የኦዲት ባለሙያዎች ሙያዊ መርህና ሞራልን ሊያስቀድሙ እንደሚገባም አመልክተዋል።       

የገንዘብ  ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው  አካላት  ጋር በመሆን  ዘርፉን ተወዳዳሪ  ለማድረግ  የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል። 

የኦዲት ዘርፉ ውጤታማ ሆኖ ለፋይናንስ ሥርዓቱ ጤናማነት አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዲኖረው ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ሂክመት አብደላ፤ ታክስ የሚከፈለው እንዲሁም ባንኮች ብድር የሚሰጡት የኦዲተሮችን ሪፖርት መነሻ አድርገው በመሆኑ ዘርፉ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ ይፈልጋል ብለዋል።   


 

በመሆኑም ቦርዱ ኦዲተሮች አቅማቸውን እንዲገነቡ ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ በአግባቡ በማይሰሩት ላይ ቁጥጥር እየተደረገ የእርምት እርምጃዎች እየተወሰደ መሆኑ አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ192 ኦዲተሮች ፈቃድ /ላይሰንስ/ መስጠቱን ጠቁመው፤ ቦርዱ ሕገ-ወጥ አሠራር የሚከተሉትን በመለየት እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተናግረዋል።

በዚህም ሐሰተኛ ሪፖርት የሚያዘጋጁ፣ ፈቃድ ሳይኖራቸው ኦዲት የሚያደርጉ ድርጅቶችና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

የውጭ ኦዲተሮች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዳንኤል ጌታነህ፤ በመስኩ ሕግን ጠብቀው የሚሰሩ ኦዲተሮች እንዳሉ ሁሉ፤ የሐሰት ኦዲት ሪፖርት የሚያዘጋጁ ቀላል ቁጥር የላቸውም ብለዋል።


 

በመሆኑም ባለድርሻ አካላትና የፍትሕ አካላት የጉዳዩን አንገብጋቢነት በመረዳት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።  

በሌላ በኩል የኦዲት ባለሙያዎች ዘመኑን የዋጁ እንዲሆኑ በቴክኖሎጂና አቅም ግንባታ ረገድ ሊታገዙ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ማኅበሩም የድርሻውን ለመወጣት እየጣረ ነው ብለዋል።

 

 

 

 

       

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም