የአፍሪካን ዲጂታላይዜሽን በማፋጠን ሂደት የሁሉም አካላት ርብርብና ጥረት ሊታከልበት ይገባል- የአፍሪካ ሕብረት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/2016(ኤዜአ)፦ የአፍሪካን ዲጂታላይዜሽን በማፋጠን ሂደት የሁሉም አካላት ርብርብና ጥረት ሊታከልበት እንደሚገባ የአፍሪካ ሕብረት ገለጸ። 

አፍሪካ ሕብረት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቴክኒካል ኮሚቴ አምስተኛ መደበኛ ጉባዔውን አካሂዷል።

አፍሪካ ሕብረት የመሠረተ-ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር ዶክተር አማኒ አቡ-ዘይድ፤ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት የአፍሪካን ዲጂታላይዜሽን የማፋጠን ሂደት የሁሉንም ርብርብ ይፈልጋል ብለዋል። 

የአፍሪካ ሕብረት ይህንን ውጥን እውን ለማድረግ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ገቢራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ አባል አገራቱም ተመሳሳይ ስትራቴጂዎችን ገቢራዊ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማፋጠን የሚከናወኑ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ለማፋጠን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።    

የአህጉሪቱን ዲጂታል ምህዳር ለማስፋት አገራት የፖሊሲ ስትራቴጂ እንዲያዘጋጁና እርስ በርስ እንዲያጣጥሙ በማድረግ ለውጦች እየታዩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጎን ለጎንም የሳይበር ደኅንነትንና የግል መረጃን ለመጠበቅ የተደረሰው ስምምነት መፅደቁን ጠቁመው፤ ይህም ካለፈው ሰኔ ጀምሮ ገቢራዊ መሆን መጀመሩን ጠቁመዋል።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ልማትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መሥራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የአፍሪካ ሕብረት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 በኢኮኖሚ ልማት፣ የማኅበረሰብ ለውጥና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ለያዘው ዕቅድ ስኬት የአባል አገራት ሁለንተናዊ ጥረትና በተለይም የዲጂታል ልማት ግንባታ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም