በኢትዮጵያ የሃይል ልማት ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን ለማሳካት የሴቶችን ጥረትና ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሃይል ልማት ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን ለማሳካት የሴቶችን ጥረትና ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 13/2016 (ኢዜአ) ፦በኢትዮጵያ የሃይል ልማት ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን ለማሳካት የሴቶችን ጥረትና ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሙድ ገለጹ።
"በኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች ማህበር" ከመንግስትና የግሉ ዘርፍ ከተውጣጡ አካላት ጋር በዘርፉ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሴቶች የሽልማት ስነ ስርአት አካሂዷል።
ከ400 በላይ አባላትን ያቀፈው ማህበር ከአራት አመታት በፊት በኢነርጂ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙያ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶችን ያካተተ ነው።
ማህበሩ በተለይ በገጠሩ የሀገሪቷ ክፍል የኃይል ተደራሽ ያልሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግም እየሰራ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሙድ፤ በኢትዮጵያ የድህነት ቅነሳ መርሃ ግብርን ለማሳካት በተለይም የኢነርጂ ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የሃይል ተደራሽነትን ማስፋትና የኢንዱስትሪ ልማትን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
በሳይንስ ቴክኖሎጂ፣ ኢነርጂና የሂሳብ ዘርፎች አሁን ላይ የሴቶች ተሳትፎ 28 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ የሴቶችን ጥረትና ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አደይ ጌታቸው፤ የማህበሩ ዋነኛ አላማ በዘርፉ የሴቶችን ሚና ማጎልበትና ለአገሪቷ የኢነርጂ ልማት እገዛ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
በሽልማት ስነ ስርአቱ ላይ በኢነርጂው ዘርፍ ተጽእኖ ፈጣሪና የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሴቶች ተሸላሚ ሆነዋል።