ዩኒቨርሲቲው ብቁ የሰው ሀይል በማፍራትና ምርምር በማካሄድ ለሀገራዊ ልማት ዕቅዶች መሳካት የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ብቁ የሰው ሀይል በማፍራትና ምርምር በማካሄድ ለሀገራዊ ልማት ዕቅዶች መሳካት የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ
ጋምቤላ፣ ህዳር 13/2016 (ኢዜአ) ፦የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ብቃት ያለው የሰው ኃይል በማፍራትና ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ለሀገራዊ ልማት ዕቅዶች መሳካት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ።
ዩኒቨርሲቲው የአጋር አካላትን ተሳትፎ በማጎልበት የመማር ማስተማርና የምርምር ሥራዎችን ለማጠናከር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ መክሯል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ አባል አቶ ቴንኩዌይ ጆክ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ለአንድ ሀገር እድገት መሳለጥ ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይልና ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወሳኝ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራትና ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር ለተያዙ የልማት ዕቅዶች ስኬታማነት የድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።
የጋምቤላ ክልል ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ የሚውል የግብርና፣ የቱሪዝም፣ የማዕድንና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤት መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው በክልሉ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ምርምር በማካሄድ የክልሉን እድገት ለማፋጠንና የማህበረሰቡን ህይወት ለመለወጥ የበኩሉን እንዲወጣ አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለሚያካሂዳቸው የመማር ማስተማርና የምርምር ሥራዎች ስኬት የክልሉ መንግስት የተቻለውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አቶ ቴንኩዌይ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዲሪባ ኢቲቻ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ በዩኒቨርሲቲው የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን ጥራቱን የጠበቀ የስልጠናና የምርምር ሥራዎች ለማከናወን ተግባራዊ እንቅስቀሴ እያደረገ ነው።
የዛሬው መድረክ ዋና ዓላማም ውጤታማ የማመር ማስተማርና የምርምር ሥራዎችን ለማካሄድ በሚደረገው ጥረት የአጋር አካላትን ትብብርና ተሳትፎ ለማጠናከር መሆኑንም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለግማሽ ቀን ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።