ቀጥታ፡

የምርምር ማዕከላቱ ምርጥ ዘርን ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን ምርታማነትን እያሳደጉ ነው

ሐረር፣ ህዳር 13/2016 (ኢዜአ)፡-በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች የሚገኙ የግብርና ምርምር ማዕከላት ምርጥ ዘርን ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን የምስራቅ ክላስተር ዓመታዊ ግምገማውን በሐረር ከተማ አካሂዷል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የግብርና ምርምር ማዕከላት ሃላፊዎች እንደገለጹት፣ የተሻሻሉ የሰብልና የቡና ዝርያዎችን ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ለአርሶ አደሩ በማስተዋዋቅ ምርታማነትን እያሳደጉ ይገኛሉ።

በ1997 ዓ.ም የተቋቋመው የመቻራ ግብርና ምርምር ማዕከል የቡና ምርታማነትን ለማጎልበት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የምርምር ማዕከሉ ሃላፊ አቶ ፈቀደ ገመቹ ይገልጻሉ።

በዚህም ማዕከሉ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ምርምር ሲያካሂድባቸው የነበሩ 4 የቡና ዝርያዎችን በምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ በባሌና አርሲ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ማሰራጨቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ባለፈው ዓመት አራት ኩንታል የቡና ምርጥ ዘር ለምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞን አርሶ አደሮች ማሰራጨቱን የጠቀሱት አቶ ፈቀደ፣ ማዕከሉ በተለይ በሰብልና በእንስሳት መኖ ላይም ምርምር እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመትም ማዕከሉ 6 ኩንታል የቡና ምርጥ ዘር እያዘጋጀ ይገኛል ብለዋል።

የተሻለ ምርት የሚሰጡ ሁለት የቦሎቄ እና የከብት መኖ ምርጥ ዘሮችም በአርሶ አደሩ ማሳ የማላመድ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የፈዲስ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሁሴን ሀብሮ እንዳሉት፣ ማዕከሉ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅ፣ ከአካባቢው አየር ሁኔታ ጋር የማላመድ እና ከአርሶ አደሩ ጋር በመሆን በሰርቶ ማሳያ ዝርያዎችን የማባዛት ሥራ እያከናወነ ይገኛል።

በሰርቶ ማሳያ ማሳ ላይ ውጤታማ የሆኑትን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ለበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት የዘር እጥረት እንዳይከሰት የዘር ብዜት ሥራ ማከናወን እንዲሁም የስንዴ መውቂያ ማሽኖችን በማዕከሉ ሰርቶ ለአርሶ አደሩ ማቅረቡን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የማር ኢኒሼቲቭን ለማጎልበት 85 የንብ ቀፎዎችን ለ3 ወረዳ አርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን የተናገሩት አቶ ሁሴን፣ በእንስሳት መኖም 40ሺህ የሚደርሱ የመኖ ችግኞችን ማከፋፈሉን ገልጸዋል።


 

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኢሳቅ ዩሱፍ በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን አርሶ አደር የግብርና ምርታማነት ለማጎልበት የሰብል ምርጥ ዘርና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እያሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በበጋ የመስኖ ስንዴ እና በእንስሳት ሃብት ልማት ምርታማነትን ለማጎልበት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ይሳቅ፣ አርሶ አደሩንም ከቴክኖሎጂዎቹ ጋር እንዲተዋወቅ መደረጉን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን የማምረት ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አርጋግጠዋል።


 

"እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2020 ጀምሮ የተለያዩ ምርትና ምርታማነት የሚያጎለብቱ የግብርና ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን አስተባባሪ ዶክተር ሳሙኤል ቱፋ ናቸው።

በዚህም በተለይ የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማትን ለማጎልበት ባከናወነው ሥራ ውጤት መመዝገቡን ነው የገለጹት።

 

የኦሮሚያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ከዚህ ቀደም የነበረውን አሰራር በመለወጥ አርሶ አደሩም ሆነ ባለሀብቱ ገበያ ተኮር ምርቶችን በፍጥነት፣ በጥራትና በብዛት አምርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም አምራቹ የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ ከማድረግ ባለፈ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ስለሚደግፍ በቀጣይም ምርትና ምርታማነትን የማጎልበት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኦሮሚያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን የምስራቅ ክላስተር ዓመታዊ ግምገማውን ትናንት ሲያካሂድ የግብርና ተመራማሪዎች፣ የምርምር ማዕከላት ሀላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮችና ሞዴል አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም