ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል አምራች ኢንዱስትሪዎች  ለማጠናከር እየተሰራ ነው

ሀዋሳ፤ኅዳር 13/2016 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋትና ለማጠናከር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የኢንዱስትሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ በየነ በራሳ አስታወቁ።

የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ዙር የምክክር መድረክ  በሀዋሳ ተካሄዷል።

ምከትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪን በማስፋፋት በሀገር ኢኮኖሚ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የተቀናጀ ጥረት እያደረገ ነው።

በክልሉ በሀገር ደረጃ የታሰበውን ብልጽግና ለማሳካት ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚከናወኑ የልማት ዘርፎች ኢንዱስትሪ አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ በክልሉም ዘርፉን ለማጠናከር  የተቋቋመው ምክር ቤት በየደረጃው ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

በ"ኢትዮጵያ ታምርት''ንቅናቄ በክልሉ በተከናወኑ ተግባራት በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመዘገበውን አመርቂ ውጤት ለማስቀጠል እየተሰራ ነው ያሉት አቶ በየነ፣ ምክር ቤቱ በንቅናቄው የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር እንደሚሰራም  አስታውቀዋል ።


 

የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሻሻሞ ቅልሲ በበኩላቸው የክልሉ የኢንዱስትሪ ልማት ምክር ቤት  ከተቋቋመ ወዲህ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮች በቅንጅት እየተፈቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ለውጭ ገበያ ካቀረቧቸው ምርቶች ከ107 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማስገኘታቸውን አስታውቀዋል።

በተለይም በ''ኢትዮጵያ ታምርት''ንቅናቄ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ባለፈው ዓመት 243 አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች መቋቋማቸውን አቶ ሻሻሞ  ተናግረዋል።

እንዲሁም  58 አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪነት ተሸጋግረዋል ብለዋል።

በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ያለውን ዕምቅ ሀብት፣ አቅምና ሀገራዊ አስቻይ ሁኔታዎች ለመጠቀም የተቀናጀ ጥረት እንደሚደረግ ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥምረት በመፍጠር ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማድረግ ሀብት ያፈሩ አርሶና አርብቶ አደሮች በኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲሳተፉና ተጠቃሚ እንዲሆኑ  ትኩረት መሰጠቱን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት የቴክኒክ አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚ አቶ አበበ እድሉ ጽህፈት ቤቱ ለኢንዱስትሪ ተቋማቱ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በፅህፈት ቤቱ በተለይ ካለፈው ዓመት ወዲህ 11 ፕሮጀክቶች ተቀርጸው የኃይል አቅርቦት ለማሻሻል ጥረት መድረጉንና በዚህም 47 አምራች ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት ችግራቸው  መቃለሉን ተናግረዋል።

ጽህፈት ቤቱ በክልሉ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ የእንጨት ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎችን በኮንክሪት ምሰሶዎች በመተካት የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

  በመድረኩ በ''ኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ በክልሉ የተመዘገበውን ውጤትና የንቅናቄውን ቀጣይነት የሚያመላክቱ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጓባቸዋል። 

የባንኮችን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችን በአባልነት ያቀፈው የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት  ምክር ቤት  በ2014 ዓ.ም እንደተመሠረተ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም