በኢንዱስትሪ ፓርኮች የኃይል ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢንዱስትሪ ፓርኮች የኃይል ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 13/2016 (ኢዜአ) ፦የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን በኢንዱስትሪ ፓርኮች የኢነርጂ ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ።
ሥምምነቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰና የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ ፈርመውታል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ሥምምነቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኃይል እንዲቆጥቡና ውጤታማ አጠቃቀም እንዲኖራቸው ያስችላል ።
ሥምምነቱ የኃይል ብክነትን በመቀነስ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመው የካርቦን ልቀት በመቀነስም አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
ባለሥልጣኑ ለኮርፖሬሽኑ የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አንስተው ሥምምነቱ የተለያዩ ፈንዶችን በማፈላለግ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
ሥምምነቱ ባለሥልጣኑ በ2030 እንደ አገር 14 በመቶ በተያዘው ዓመት ደግሞ 4 በመቶ ኃይል ለመቆጠብ የያዘውን ውጥን ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑንም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
የኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው ሥምምነቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኃይል እንዳያባክኑና ውጤታማ አጠቃቀም ገቢራዊ ለማደረግ ያስችላል ብለዋል።
በሥምምነቱ መሰረት፤ የተለያዩ የኢነርጂ አጠቃቀም ማሻሻያ ዘዴዎችን በመጠቀም የኮርፖሬሽኑን ዓመታዊ የኢነርጂ ፍጆታ በ10 በመቶ ለመቀነስ ያስችላልም ነው ያሉት።