ቀጥታ፡

የህፃናት መጻህፍት ተደራሽነት ትኩረት ይሻል - የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

አዳማ ፤ ህዳር 13/2016 (ኢዜአ) ፦ የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናት አገራቸውን በአግባቡ አውቀው እንዲያድጉ ለማስቻል የህፃናት መጻህፍት ዝግጅት እና ተደራሽነት ትኩረት እንደሚያስፈልገው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለፀ።

በኢትዮጵያ የህፃናት መጻሕፍት ዕድገትና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ ተካሂዷል።

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነጥበብ፣ ስነ ጥበብና ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሃድ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት የነገ ሀገር ተረካቢ ልጆችን በግብረ ገብነትና በስነ ምግባር ለማነፅ የህፃናት መጻህፍት ልማትና ዕድገት ሚናው የጎላ ነው።

ልጆች ከህጻንነታቸው ጀምሮ ባህላቸውን፣ ታሪክና ማንነታቸውን አውቀው እንዲያድጉ ከማስቻል አንፃር የህፃናት ስነ ጽሑፍ ልማት ላይ በትብብር መስራት አለብን ብለዋል።

በተለይም የህፃናት ለውጭ ባህል መጋለጥ፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋን ብቻ እንዲናገሩና በቤት ውስጥ የውጭ ፊልሞችን እንዲመለከቱ በቤተሰብ ጭምር ግፊት መኖሩ ትውልዱ የራሱን ባህል፣ ታሪክና ማንነት እንዲዘነጋው እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ልጆች በሀገራቸው ማንነትና ታሪክ ውስጥ በዕውቀት እንዲያድጉ ባለድርሻ አካላት በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በትብብር መስራት አለብን ብለዋል።

የትውልድ ክፍተት እንዳይፈጠር በህፃናት መጻህፍት ልማትና ዕድገት ላይ በጋራ ለመስራት ቀጣይ የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አመልክተዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ የህፃናት መጻህፍት ዕድገትና ተግዳሮቶች ዙሪያ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ይታገዙ አጥናፉ በበኩላቸው የህፃናት ስነ ጽሁፍና የልጆች መፅሐፍ ልማት ላይ በሚፈለገው ልክ አለመሰራቱን አንስተዋል።

በተለይም መጻህፍቱ ሊኖራቸው በሚችሏቸው ይዘትና ዝግጅት፣ የቋንቋ ዕውቀት፣ ባህል፣ ማንነትና የህፃናት የዕድገት ሁኔታዎች በአግባቡ የተቃኙ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

ለዚህም የዘርፉ ደራሲያን ተገቢውን ዕውቀት እንዲኖራቸው በዩኒቨርሲቲዎችና የስልጠና ማዕከላት ተገቢውን የህፃናት መፅሐፍ ዝግጅት ዕውቀት፣ ክህሎትና አቅም መገንባት የሚችሉበት አሰራር ሊፈጠር ይገባል ነው ያሉት።

በዚህም የህፃናት መጻህፍት በተለያየ ይዘትና ቅርፅ ታትመው ተደራሽ መሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዚህም መጻህፍቱ ለልጆች የንባብ ልምምድና መዝናኛ የሚውሉ በተለያዩ ይዘቶችና ቅርፅ መታተም እንደሚገባቸው ጠቅሰው፤ ለዚህም መንግሥትና በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት ትኩረት መስጠት አለባቸው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም