ቀጥታ፡

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ109 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 13/2016 (ኢዜአ) ፦ በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ109 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የ2016 የመጀመሪያ ሩብ በጀት ዓመት የመንግሥት የሥራ አፈጻጻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 529 ቢሊዮን ብር ግብር ለመሰብሰብ እቅድ ተቀምጦ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ 110 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብሩን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 109 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብሩን በመሰብሰብ የእቅዱን 99 ነጥብ 2 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎች እንዲሁም ጥብቅ የክትትልና የቁጥጥር ስራ ተግባራዊ መደረጉ ለእቅዱ መሳካት አይነተኛ ሚና መጫወቱንም ነው ያስረዱት።፡

በሩብ ዓመቱ የታየው አፈጻጸም በዘርፉ ያለውን አሰራር ማዘመንና የክትትልና የድጋፍ ስራዎችን በማጠናከር የዓመቱን እቅድ ማሳካት እንደሚቻል ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ገቢ የመሰብሰብ አቅም አሁንም ይበልጥ ማደግ እንደሚችል ማሳያ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

ከዚህ አኳያ በቀጣይ በተለይ የግብር አሳበሰቡን ዲጂታላይዝ በማድረግ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በግምገማው አቅጣጫ መቀመጡንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም