ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት መወጣቱን አጠናክሮ ይቀጥላል-ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት መወጣቱን አጠናክሮ ይቀጥላል-ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 13/2016 (ኢዜአ) ፦የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የህዝብን ሰላም የማስጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት መወጣቱን አጠናክሮ መቀጠሉን የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራትና ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት መጠበቅም ያላትን ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።
ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገራዊ ግዴታውን በመወጣትና የህዝብን ሰላም በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም ሰራዊቱ ከምንግዜውም በላይ የላቀ ወታደራዊ አቅም ፈጥሮ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ተደራጅቶ የሀገር አስተማማኝ አለኝታ ሆኖ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስከበር፣ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ ያለ ብቁ ሰራዊት መገንባቱንም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናዊና በዓለም ወታደራዊ ዲፕሎማሲ ቁልፍ ስፍራ እንዳላት የገለጹት ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ፤ ከአፍሪካ እስከ ኮሪያ የዘለቀ የሰላም ማስከበር ወታደራዊ ተልዕኮው አሁንም በላቀ ብቃት ቀጥሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ ዲፕሎማሲ በመተማመንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የጠቀሱት ሜጀር ጀነራሉ፤ ከዚህ አኳያ ሰፋፊ ወታደራዊ የትብብር ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የሀገርን ክብርና የተቋሙን ዝና ማጉላት የተቻለ መሆኑን ገልጸው የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትና የቀጣናው ሰላም እንዲረጋገጥ አርዓያነት ያለው ተግባር በማከናወን ላይ እንደምትገኝም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ተምሳሌታዊ ወታደራዊ ተልዕኮ ከጎረቤት አገራት ባሻገር ዓለም የሚገነዘበውና የሚያደንቀው በመሆኑ ተልዕኮው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።